ደቡብ ሱዳን የናይል የተፋሰስ ማዕቀፍ ስምምነትን ተቀብላ ማፅደቋ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን የተቃወሙትን የ2010 የናይል ቤዚን ስምምነት ደቡብ ሱዳን እንድትፈርም መጠየቋ ይታወሳል፡፡በወቅቱ መቀመጫውን ደቡብ ሱዳን ጁባ ካደረገው አይ ከተሰኘው ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ምክትል ሀላፊ ዘላለም ብርሃን አለሙ ባለ ትንሽ ዕድሜዋ ሀገር ስምምነቱን ብትፈርም ተጠቃሚ እንደምትሆን ሱዳን ፖስት ዘግቦ ነበር፡፡

እንደ ሱዳን ፖስት ዘገባ ምክትል ሀላፊው ደቡብ ሱዳን ይህን ስምምነት ተቀብላ በመፈርም ከወንዙ በረከት ተቋዳሽ መሆን ትችላለች፡፡አሐዱ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን እንድትፈርም ስለምን አጥብቃ ፈለገች የሚለውን ጥያቄ ለወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት አማካሪው አቶ ተፈራ በየነ አቅርቧል፡፡ ይህ ስምምነት ፀድቆ ተግባራዊ የሚሆነው ስድስት ሀገራት ተቀብለውት ፊርማቸውን ሲያኖሩበት እንደሆነ የገለፁት አማካሪው ይህ እንዲሆን ደግሞ ሀገሪቱ መፈረሟ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ የተፋሰሱን ሀገራት እኩል ተጠቃሚ ከማድረጉ አኳያ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ብትፈርምላት በጎ ጎኑ ያመዝናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህን ስምምነት እስካሁን አራት ሀገራት ተቀብለው ፊርማቸውን እንዳኖሩም ገልፀዋል፡፡ደቡብ ሱዳን ይህን ስምምነት ተቀብላ ለማፅደቅ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2012/13ዓ.ም እንቅስቃሴ የጀምረች ቢሆንም በወቅቱ ተነስቶ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ይህን እውን ማድረግ ሳትችል ቀርታለች፡፡

ቀን 29/06/2013

አሐዱ ራዲዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply