ደቡብ አፍሪካ ወደ አምስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበል መግባቷ ተነገረ::

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2014 ደቡብ አፍሪካ ወደ አምስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበል መግባቷ ተነገረ:: ደቡብ አፍሪካ ወደ አዲስ የኮቪድ- 19 ማዕበል እየገባች መሆኑን የሀገሪቱ የወረርሽኝ ምላሽ እና ፈጠራ ማዕከል አስታውቋል። የቤታ እና ኦሚክሮን ልውጥ ባህሪ ያላቸውን ቫይረሶችን በመለየት ዝነኛ የሆነው የጥናት ማዕከል ሃላፊ አምስተኛው ዙር የወረርሽኝ ስርጭት መከሰቱን በትዊተር ገፁ ላይ ይፋ በማድረግ አስጠንቅቋል።

ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ በኮቪድ -19 በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቁ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን በጥንቃቄ ጉድለቶች ሳቢያ ወረርሽኙ በአዲስ መልክ እንዲያገረሽ ሆኗል ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የብሄራዊ ተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት በ24 ሰአታት ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ካለፉት ጥቂት ቀናት ጋር ሲነጻጸር እየጨመረ መምጣቱን ይፋ በማድረግ የሚሞቱና ወደ ሆስፒታል የሚያመሩ ሰዎች መጠን ከፍ ማለቱን ገልጿል፡፡

የወረርሽኙን የስርጭት ሁኔታ ተከትሎ በቅርብ ቀናት ውስጥ እየተመዘገቡ ያሉ አሃዞች ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ ከፍተኛ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ከነበረው ደግሞ በእጅጉ የላቀ ነው ተብሏል። የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስቴርም ባለፈው ሳምንት የቫይረሱ ስርጭት እንደገና ከፍ ማለት እንዳሳሰበው
መግለፁ ይታወሳል ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ካላት ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ውስጥ ከ45 በመቶ በታች ያህሉ አዋቂዎች ብቻ ሙሉ ክትባት የወሰደ መሆኑ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply