
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ 18 ትምህርት ክፍሎችን መዝጋቱ በዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ተቃውሞ አስነሳ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሀምሌ 1/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ከአማርኛ ቋንቋ፣ ከታሪክ፣ ከማንነት፣ ከባህል እና ከአገር በቀል እውቀቶች ጋር የተያያዙ የማኅበራዊና ሥነ ሰብ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ሳይንስ እና የስነ ትምህርት ኮሌጆችን መዝጋቱ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ ዩኒቨርስቲው በአራት ኮሌጆች ሥር የሚገኙ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ድግሪ የሚሰጡ 18 ትምህርት ክፍሎችን መዝጋቱን ተከትሎ፤ የዩኒቨርስቲው መምህራን የተቃውሞ ደብዳቤ ለደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አስተዳርር ጽ/ቤት አስገብተዋል፡፡ መምህራኑ ለቦድሩ ባስገቡት ደብዳቤ የዩኒቨርስቲው አመራር “በልየታ እና በልህቀት ማዕከል ያልተካተቱ ናቸው” በሚል ሰበብ በማኅበራዊ እና በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጆች ሥር የሚገኙ ትምህርት ክፍሎችን፣ እንዲሁም የሕግና የሥነ ትምህርት ኮሌጆችን እንደሚዘጋ እና መምህራኑንም ከሥራ እንደሚያግድ አሳውቆናል ብለዋል፡፡ መምህራኑ በደብዳቤያቸው ውሳኔውን ኢ-አመክኗዊና ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው ያሉት ሲሆን፤ የአማርኛ ትምህርት ክፍል እና የትምህርት ክፍሉ መምህራን ከሐምሌ 1/2015 ጀምሮ የሥራ ስንብት ደብዳቤ እንደሚደርሳቸው ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር መምህራንና፣ ተማሪዎችን፣ እንዲሁም የዞኑን ማኅበረሰብ እና ባለድርሻ አካላትን ሳያወያይ፤ የፌዴራል እና የክልሉን የሥራ ቋንቋ በማን አለብኝነት እና በንቀት መዝጋቱ ተገቢነት የሌለው ውሳኔ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስዱ መምህራኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዘጋቸው የትምህርት ክፍሎች ጋር በተያያዘ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ገለጻ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ በዩኒቨርሲቲው የመምህራን ማኅበር ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል ተብሏል፡፡ እንዲሁም በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊሸፈኑ የማይችሉትን የማኅበራዊና ሥነ ሰብ፣ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ እንዲሁም የሥነ ትምርት ኮሌጆችን ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ባልዘጉበት ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲው እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ፍላጎትና ምርጫ ውጪ በጥድፊያ እንዱዘጉ መደረጉ፣ በክረምት ፕሮግራም ብቻ ከ18 ሺሕ በላይ ተማሪዎች እንዳይማሩ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ታሪክ ጥናት ማዕከልን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተቋቋሙትን የባህል ማዕከል መዝጋቱን የተቃወሙት መምህራኑ፤ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ስለ ውሳኔው በግልጽ መረጃ እንዲሰጥና የተዘጉ ት/ት ክፍሎች እንዲከፈቱ ጠይቀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ ጥያቄ የተነሳበት ውሳኔ በትምህርት ሚኒስቴር የተወሰነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ “ትምህርት ሚኒስቴር በጥናት በወሰነው መሰረት ወደ ሌላ ዩኒቨርስቲ ሽግሽግ ይደረጋል እንጂ ከሥራ የሚሰናበት መምህር የለም።” የሚል ምላሽ ስለመስጠታቸው የዘገበው አዲስ ማለዳ ነው።
Source: Link to the Post