“ዲጂ ትራክ” የተሰኘ ተንቀሳቃሽ ዘመናዊ የስልጠና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ረቡዕ ኀዳር 7 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ትምህርት ሚኒስቴር ከሁዋዌ እና ከ ‘Icog Anyone Can Code’ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መስጠት የሚያስችል “ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ” የተሰኘን ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል።

ፕሮጀክቱ “ዲጂ ትራክ” የተሰኘውን ተንቀሳቃሽ ዲጂታል መማሪያ ክፍል በመጠቀም፤ በገጠር እና በሩቅ አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ መጀመሩ ተገልጿል።በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው በዚሁ የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይም፤ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ሮ)፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የሁዋዌ እና ከ’Icog Anyone Can Code’ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።በመርሃ ግብሩ ላይም ትምህርት ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በጋራ ሊሰሩ ከሚችሉ አካላት ጋር ትብብር በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፤ ከሁዋዌ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኢትዮጵያ እና ከ’Icog Anyone Can Code’ ጋርም የተደረገው የአጋርነት ሥምምነት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።አክለውም፤ ፕሮጀክቱ በተለይም የቴክኖሎጂ እና የኔትወርክ ተደራሽነት በሌለባቸው የአገራችን አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች፤ በፈጠራ ሥራዎች እንዲነቃቁና የዲጂታል ቴክኖሎጂው ያመጣቸውን ለውጦች እንዲያጣጥሙ ይረዳቸዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።የሁዋዌ የሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር ሊዮ ሊዮ በበኩላቸው፤ ሁዋዌ በመላው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ክህሎቶችን ማዳበር የሚችሉበትን መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህም ፕሮጀክት የመርሃ ግብሮቹ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም የ”ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ከኮምፒዩተር፣ ከፕሮግራሚንግ፣ ከኢንተርኔት ዘርፎች እና ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቁ ለማስቻል ተቅዶ የተዘጋጀ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።“ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ሳስብ እኔ በልጅነቴ ያገኘሁትን ዕድል ለሌሎች ለመስጠት ለመሞከር ነው።” ያሉት ደግሞ የ’Icog Anyone Can Code’ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሔም ደሴ ሲሆኑ፤ የ21 ኛው ክፍለ ዘመን መሰረታዊ ችሎታዎች መግቢያ የሆነውን የቴክኖሎጂ ትምህርት፤ ዛሬ ለወጣቶች በጣም አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህም እድል ለወጣቶች የሚፈጥረው የእውቀት ነፃነት ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል።

“ዲጂ ትራክ” ቀጣዩን ኮድ አድራጊ ትውልድ በማነሳሳት የአገሪቱን የቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርፁ የፈጠራ ባለሙያዎችን ያገነባል ያሉት ቤቴልሄም፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ ህፃናትን እና ወጣቶችን በዲጂታል እውቀት ለማሳደግ እና በሮቦቲክስ ላይ ለማስተማር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይይዛልም ብለዋል።“ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ” የላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን፣ ሮቦቲክ መሳሪያዎችን እና ማይክሮ ኤሌክትሮኒክስን ጨምሮ የተማሪዎችን የመማር ማስተማር ሂደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚያደርሱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የተገጠመለት እና የስልጠና ማዕከል በመሆን የሚያገለግል ኮንቴነር ሲሆን፤ ለተከታታይ 7 ዓመታት በ9 የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ሀገር አቀፍ የቴክኒክ ጉብኝት እንደሚያደርግ በመድረኩ ተነግሯል።

ጉብኝቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚካሄደው ስለ STEAM (ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ አርት እና ሂሳብ) ትምህርት ፋይዳ ግንዛቤን የማስጨበጥን አላማን በማንገብ ነው።

የ”ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ” ፕሮጀክት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመመስረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ትምህርት ዘርፍ፣ የመጀመሪያ ደረጃ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት እና የዲጂታል ክህሎትን በመደገፍ፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና የህብረተሰብ መሻሻል ላይ የራሱን የሆነ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ያጠበቃል።

The post “ዲጂ ትራክ” የተሰኘ ተንቀሳቃሽ ዘመናዊ የስልጠና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply