ዳሌ ምንድነዉ?

በአከርካሪያችን እና በሁለት እግሮቻችን መሃከል ያለ ፤የታችኛዉ የወገባችንን ክፍል ከእግራችን ጋር የሚያገጣጥም እና የመራቢያ አካላት፣ ማህጸን የሽንት ፊኛን የሚሸከም አካል ነዉ፡፡

ዳሌ ላይ ከሚያጋጥሙ ጉዳቶች መካከል የዳሌ ዉልቃት /ስብራት አንዱ ነዉ፡፡

ጣቢያችን ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 ስለ ዳሌ ዉልቃት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመገጣጠሚያዎች እና ቀዶ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶክተር ገለታዉ ተሰማ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የዳሌ ዉልቃት/ስብራት እንዴት ይከሰታል?

 • በተለያዩ አደጋዎች ይከሰታል፡፡ ከባድ ነገር እላያችን ላይ ሲወድቅ ይከሰታል፡፡
 • በተለይ ደግሞ ቤት የሚያፈርሱ ሰዎች ለዚህ የበለጠ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡
 • የመኪና አደጋ ደግሞ ሌላዉ ምክንያት ነዉ፡፡
 • የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ጥንቃቄ አለመኖር፡፡
 • ወደ ክፍለአገር ሲወጣ ደግሞ ከዛፍ ላይ መዉደቅ፤ ወደ ገደል መዉደቅ እንደ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
 • የዳሌ ዉልቃት ሲያጋጥም ታዲያ ከሆዳችን ወደ እግራችን የሚወርዱ የተወሳሰቡ የደም ስሮች በመኖራቸዉ እና በዚህም የመድማት ሁኔታ ስለሚከሰት ብዙዎቹ በቦታዉ ህይወታቸዉ የማለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነዉ፡፡
 • ሆዳችን ዉስጥ ሳምባ፣ጉበት ፣ ኩላሊት ፣ጣፊያ፣ አንጀታችን ላይ ጉዳት፣ የሽንት ፊኛም ሊቀደድ ይችላል፡፡
 • በዚህ ሰዓት ደም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚፈስ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡፡
 • የዳሌዉን አቃፊ በጨርቅ መያዝ አለመቻል በሰዉነታችን ዉስጥ ያለዉ ደም ፈሶ እንዲያልቅ ማድረግ ነዉ በዚህም ህይወት የማለፍ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ነዉ ባለሙያዉ የገለጹት፡፡
 • የሚያጋጥመን አደጋ የሚያስከትለዉ ዉልቃት ብቻ ሊሆን ይችላል አልያም ስብራት ሊሆን ይችላል አንዳንዴ ደግሞ ሁለቱም ሊሆኑ ይችላል፡፡

ምልክቶቹ ምንድናቸዉ?

 • የማያቆም ከፍተኛ ህመም ይኖራል፡፡
 • እግራቸዉ ወይም ዳሌያቸዉ አከባቢ የቅርጽ ለዉጥ ይኖራል፡፡
 • እግራቸዉ ሊዞር ይችላል፡፡ የዳሌያቸዉ አቃፊም ቦታዉን ሊቀይር ይችላል፡፡
 • መድማት ከዉጪ ልናይ እንችላለን፡፡ መድማት ላይኖርም ይችላል፡፡
 • ከወገብ በታች ስሜት አለመሰማት/ፓራላይዝድ/ መሆን እና
 • ከፍተኛ ደም ስለሚፈሳቸዉ ደግሞ እራስን መሳት እና እራስ አለማወቅ ሊኖር ይችላል፡፡

የዳሌ ዉልቃት በምን ይስተካከላል?

 • የመጀመሪያዉ ወደ ጤና ተቋም መሄድ መሆኑን ባለሙያዉ ይናገራሉ፡፡
 • ዳሌዉ ብዙ ጊዜ በአደጋ ምክንያት ስለሚከፈት ባገኘነዉ ጨርቅ በወገባችን ዙሪያ የላይኛዉ የእግራችን ክፍል ድረስ ማሰር አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ፡፡
 • ይህንን ማድረጋችን ደግሞ ደም በቀላሉ እንዳይደማ እና የደማዉንም እንዲረጋ ያደርገዋል፡፡
 • ቀጥሎ ደግሞ የራጅ እና የሲቲ ስካን ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡
 • ዉልቃት ከሆነ በቀላሉ ስቦ ማስገባት ይቻላል፡፡
 • ዉልቃት እና ስብራት ከሆነ ግን ስብራቱ መያያዝ መቻል አለበት፡፡
 • ዳሌ አከባቢም ከሆነ ብረት በማስገባት ከአከርካሪ ጋር ማገናኘት ይቻላል፡፡
 • አብዛኞቹ የዳሌ ዉልቃቶች የሚታከሙ ናቸዉ የሚሉት ዶክተር ገለታዉ፤በቶሎ ወደ ጤና ተቋም ስለማይመጡ ግን ህይወታቸዉ የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ብዙ ነዉ ብለዋል፡፡
 • ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ የደም መርጋት ስለሚያጋጥም እና የረጋዉ ደም ደግሞ ወደ ሳምባችን ስለሚሄድ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ህይወት ያልፋል፡፡

ህክምናዉ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?

 • የዳሌ ስብራት ወሰብሰብ ያለ ህክምና የሚያስፈልገዉ መሆኑን ዶክተር ገለታዉ ይናገራሉ፡፡
 • ብዙዎቹ እስከ ሶስት ወራት ድረስ በተጎዳዉ በኩል መርገጥ ላይችሉ ይችላሉ፡፡ በተለይ በሁለቱም እግራቸዉ ላይ ተከስቶ ከሆነ ደግሞ በዊልቼር ላይ ሊሆኑ ግድ ይላቸዋል፡፡
 • አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አደጋዉ እንደደረሰ ወዲያዉ መራመድ የሚጀምሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቀላል ዉልቃት ከሆነ እና ስብራት ከሌለዉ በነጋታዉ መራመድ የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡
 • እንደ ጉዳቱ መጠን የመንቀሳቀሻ ግዜያቸዉም ረጅም እና አጭር ሊሆን ይችላል፡፡
 • በጣም ጥቂት ሰዎች ግን ከዛ በላይ ጊዜ ሊወስድባቸዉ ይችላል፡፡ የዳሌ ስብራቱ ሲያጋጥም በጣም ከፍተኛ ሃይል ባለዉ አደጋ ስለሆነ ስብራቱ ከአንድ እና ሁለት በላይ ስለሚሆን ያንን ለመጠገን ጊዜ ይወስዳል፡፡
 • የተለመደዉ ግን ከሶስት ወር እና ከዛ በላይ ነዉ፡፡
 • ህክምናዉን ያገኙ ሰዎች ከሶስት ወር ጀምሮ መንቀሳቀስ ይጀምራሉ ሲሉ ባለሙያዉ ነግረዉናል፡፡

ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply