ዳሸን ባንክ “ዱቤ አለ” የተሰኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት ጀመረ

   ዳሸን ባንክ “ዱቤ አለ” የተሰኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት ጀመረ

ዳሸን ባንክ ከኤግል ላይን ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር “ዱቤ አለ” የተሰኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዱቤ ግብይት አገልግሎት  ባለፈው ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም  በሸራተን አዲስ ሆቴል አስተዋውቋል፡፡  
 “ዱቤ አለ” በሀገራችን በባህላዊ መንገድ ሲከናወን የነበረውን የማህበረሰባችንን የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አስተማማኝ የባንክ አሰራር በማገዝ የቆየን እሴት የሚያስቀጥል የግብይት አገልግሎት መሆኑን  የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በማስጀመሪያ ሥነስርዓቱ  ላይ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ  ዳሸን ባንክ ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በመተባበር፣ ህብረተሰቡ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችንና በርካታ አገልግሎቶችን በ3 ወር፣ በ6 ወርና በ12 ወር በሚመለስ ዱቤ በወለድና ያለወለድ መግዛት የሚያስችል አማራጭ መሆኑም ተብራርቷል፡፡
“ዱቤ አለ” ሸማቾች የፈለጉትን እቃ በዱቤ ገዝተው ቆይተው መክፈል የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ አሰራርና መተግበሪያ ሲሆን፤ መተግበሪያውን በቀላሉ ከፕሌይስቶር ወይም ከአፕስቶር በማውረድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻል የኤግል ላይንስ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በእርሱ ፈቃድ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡   “ዱቤ አለ” የተሰኘው የዱቤ  ግብይት አገልግሎት ህብረተሰቡ ያሻውን በዱቤ ገዝቶ ቀስ ብሎ መክፈል የሚችልበትን እፎይታ ይሰጣል የተባለ ሲሆን፤ የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና በማቅለል በኩልም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጧል፡፡
የኤግል ላይንስ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈፃሚው በእርሱ ፈቃድ ጌታቸው ቴክኖሎጂውን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት ሲደረግበት ቆይቶ በሀገር ልጆች እንዲበለፅግ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ደንበኞች መተግበሪያውን ካወረዱ በኋላ መመዝገብ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ከተመዘገቡ በኋላ ወደ ዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ የዱቤ ገደብ ማስፈቀድና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ታውቋል፡፡     

Source: Link to the Post

Leave a Reply