
ዶክተሮች ያዘዙት የህክምና ማስረጃ እንዳላቸው የገለጹት ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ አግባብ ያልሆነው እግድ ተነስቶ ህክምናቸውን እንዲከታተሉ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ ምን አሉ? የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ ፤ ከሀገር ውጭ ህክምናዬን እንዳልከታተል ያገዱ አካላት ለምን እንዳገዱ ምክንያት የላቸውም ፤ ህክምናዬን በአፋጣኝ ካላደረኩ ቀኝ እግሬን እስከማጣት ሊያደርሰኝ ይችላል ብለዋል። ቀደም ሲል በእርስ በእርስ ጦርነት የጥይት ምት እንዳለባቸው የገለፁት ጄነራሉ በተለያዩ ምክንያቶች በአግባቡ ህክምና እንዳልተከታተሉ ገልጸዋል። እግራቸው ውስጥ ወደ 8 የሚደርሱ ፍንጣሪዎች መሰግሰጋቸውን የገለፁት ጄነራል ተፈራ ፤ እየቆየ ሲሄድ ነርቫቸውን በተደጋጋሚ እየነኩ መሆናቸውን እና የህክምና ባለሞያዎች የተሻለ ህክምና ካላገኙ እየከፋ እንደማሄድ እንደገለፁላቸው አስታውሰዋል። ለዚሁ ህክምና ወደ እስራኤል ሀገር ለመሄድ ስርዓቱን ጠብቀው ያለውን ነገር ጨርሰው ሊወጡ ሲሉ መከልከላቸውን አስረድተዋል። ብ/ጄነራል ተፈራ ፥ ” ዓላማዬ ህክምና ነበር ምንድነው ምክንያቱ ብዬ ስጠይቅ ‘ እንድትወጣ አልተፈለገም ‘ የሚል መልስ ሰጡኝ። በዛ ምክንያት ጉዞው ተደናቀፈ ፤ አሁን ህመሙ እየጨመረ መጥቶ አላንቀሳቅሰኝ አለ ፤ የነርቭ ስርዓቴም እየተነካ በመሆኑ ለመርገጥም ተቸግሬያለሁ ፤ አንዳንዴ እስከ ጉልበቴ ድረስ ይሰማኛል ” ብለዋል። አክለው ፤ ” ገንዘብ ስጡን አላልነም ፣ እኔ ሄጄ መታከም አለብኝ ነው። ለምን እንደሚያግዱ እንኳን ምክንያት የላቸውም ፤ ምንድነው ምክንያቱ ለማገድ ? ህክምና ማግኘት ያለብኝን ማግኘት አለብኝ ምንድነው ምክንያታቸው ፤ ሰው ቢሰቃይ ይደሰታሉ እነዚህ ሰዎች ፤ አሁን መሄድ የለበትም ብለው ነው ከፃፉት አለ ማስረጃው ምንድነው ምክንያታቸው ወደዚህ አይነት ነገር ለምንድነው የሚገቡት ፤ መታከም አለብኝ ጤንነት የመብት ጉዳይ ነው ጤንነቴ አደጋ ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች በሌላ ሰው ቁስል ይደሰታሉ እንዴ ? ምንድነው የሚያስደስታቸው ? እነዚህ ናቸው ሀገር እየመሩ ያሉት ሀገር ሲመራ ሰፋ ብሎ በእኩልነት አይቶ እንጂ ካገኘው ከግለሰብም ከዚያም ጋር እየተናከሰ ነው እንዴ የሚሄደው ? ” ሲሉ ተናግረዋል። ብ/ጄነራል ተፈራ ፥ አትሄዱም ብሎ የከለከላቸውን ኃላፊ ” ለምንድነው የማልሄደው ? ” ብለው እንደጠየቋቸውና ኃላፈው ሄደው እንዲታከሙ እንደሚፈልጉ ነገር ግን ከላይ ያሉት አካላት እግዱን እንደጣሉ እንደነገሯቸው አስረድተዋል። ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ ዶክተሮች ያዘዙት የህክምና ማስረጃ እንዳላቸው ገልጸው አግባብ ያልሆነው እግድ ተነስቶ ህክምናቸውን እንዲከታተሉ እንዲደረግ ብለዋል። “መንግስት ሆደ ሰፊ መሆን አለበት ምክንያቱም ሀገር ነው እየመራ ያለው ” ያሉት ብ/ጄነራሉ ” ከግለሰቦች ጋር በሚደረግ ንትርክ ርቀት መሄድ አይቻልም የምለው ነገር ቀና ቢሆኑና ህክምናውን በወቅቱ ብወስድ ምክንያቱም ህግ እና ስርዓት አለ በዚህ መሰረት ሄጄ ታክሜ ምመጣበት እድል ቢፈጠር ይሄን ያለምንም ነገር እንደ በቀል ባይወስዱት ” ብለዋል። ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ ከባለሃብቶች ለህክምና ወጪያቸው እገዛ ይፈልጉ እንደሆነ ተጠይቀው ” ባላሃብቶች ለኔ ከሚያደርግ ስራ ላጣው ወጣት የስራ ዕድል ይፍጠር እኔ በራሴ እታከማለሁ የወጭ ጥያቄ አይደለም እኔ የምፈልገው እንድታከም እድሉን ላግኝ ነው ” ብለዋል። ይህ የብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ ቃል የተወሰደው “መድሎት” ለተሰኘ የማህበራዊ ሚዲያ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ ስለመሆኑ ጠቅሶ ኢትዮ ኒውስ አጋርቷል።
Source: Link to the Post