ዶ/ር ደብረፅዮንን ጨምሮ የ39 የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት ተነሳ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶክተር ደብረፅዮንን ጨምሮ የ39 የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ትላንት ወሰነ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ አቶ አባይ ፀሃዬ፣ አምባሳደር ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ዶ/ር መብራህቱ መለስ ጨምሮ የ39 የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ትላንት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የቀረበለትን ያለመከሰስ ይነሳልኝ ጥያቄ መሰረት በሙሉ ድምጽ ነው ያፀደቀው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫላ ለሚ ግለሰቦቹ ከፍተኛ የአገር ክህደት በመፈጸም ወንጀል፣ በሕገ-መንግስትና በሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ በሚፈጸም ወንጀል መጠርጠራቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የጦር መሳሪያ ይዞ በማመፅ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመጉዳት ወንጀል፣ በሽብርና በሌሎች የዋና ወንጀል አድራጊነት በመጠርጠራቸው ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን እንዲያነሳ ተጠይቋል።

የትግራይ ክልል መንግስት ግን ተወካዮቹ ከፌደራል መንግስት ፓርላማ እና ፌደሬሽን ምክር ቤት ”የመንግስት ዕድሜው ከመስከረም 25 ጀምሮ አብቅቷል” በሚል ማንሳቱ ይታወቃል። ከዛ በኋላ በፌደራል መንግስት የሚወሰነው ውሳኔ በትግራይ ክልል ሆነ ተወካዮቹ ተፈፃሚነት የለውም እንዳለም የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በትላንት ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አቶ ፍቅረ ገብረሕይወት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባል እንዲሆኑ ያቀረቡትን ሹመት በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

አቶ ፍቅረ በፈቃዳቸው ከቦርዱ አባልነት የለቀቁት ዶ/ር ጌታሁንን ተክተው የሚሰሩ ይሆናል።

ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቶ አፅድቆታል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply