ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነርነታቸው በመጪው ሐምሌ ወር ሊሰናበቱ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

ብሔራዊውን የሰብዓዊ መብት ተቋም ለአምስት አመታት በዋና ኮሚሽነርነት ያገለገሉት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከመጪው ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ሊሰናበቱ ነው። የዶ/ር ዳንኤል ተተኪ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከሚሾም ድረስ፤ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን  በምክትል ኮሚሽነርነት የሚያገለገሉት ራኬብ መለሰ ኃላፊነቱን እንደሚረከቡ ተገልጿል።

በ2000 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማቋቋሚያ አዋጅ፤ የዋና ኮሚሽነሩም ሆነ የሌሎች የዘርፍ ኮሚሽነሮች የስራ ዘመን አምስት ዓመት እንደሆነ ይደነግጋል። ኮሚሽነሮቹ የስራ ዘመናቸው ካበቃ በኋላ በድጋሚ ሊሾሙ እንደሚችሉ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

በመጪው ሐምሌ 24፤ 2016 የስራ ዘመናቸው የሚያበቃው ዶ/ር ዳንኤል፤ በቀጣይ ምን ሊሰሩ እንዳሰቡ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ “ምንም አልወሰንኩም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “የሚቀጥለው ስራዬ ምን እንደሆነ ገና አላወቅኩትም ግን ኮሚሽኑን ማገዜ አይቀርም” ሲሉም አክለዋል።

ዶ/ር ዳንኤል የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ሆነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት በሰኔ 2011 ዓ.ም ነበር። ምክር ቤቱ ብሔራዊውን የሰብአዊ መብት ተቋም እንዲመሩ የሾማቸው፤ ለቦታው በዕጩነት ከቀረቡ 88 ግለሰቦች ጋር አወዳድሮ ነበር። 

የአምስት አመት የስራ ዘመናቸውን እንዴት እንደሚገልጹት ለተጠየቁት ዶ/ር ዳንኤል ሲመልሱ፤ “ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋም የመመስረት ሂደት ውስጥ አብሬ ሰርቼያለሁ ብዬ አምናለሁ። ቢያንስ አንድ ጠንካራ ሰብአዊ መብት ተቋም ተመስርቷል” ብለዋል። 

ዛሬ አርብ ሰኔ 28፤ 2016 በኢሰመኮ ዋና ጽህፈት ቤት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ዶ/ር ዳንኤል ይህንኑ በድጋሚ አስተጋብተዋል። በኮሚሽኑ በነበራቸው የስራ ዘመን ከተቋሙ ሰራተኞች እና ከሌሎችም አካላት ጋር “በአንድነት” መስራታቸውን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “ጠንካራ የሆነ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም የመሰረትን ስለሆነ፤ የሰብአዊ መብት ስራችን ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ የጸና ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply