ጄፍሪ ፌልትማን ሐሙስ አዲስ አበባ ይገባሉ

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ከነገ በስተያ ሐሙስ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በስልክ በሰጡት የማክሰኞ መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።

አምባሳደር ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱት በሰላም ድርድር ጉዳይ ላይ ለመነጋገር መሆኑን ፕራይስ ገልፀዋል።

ፌልትማን ወደ ትግራይ ይሄዱ እንደሆነም ፕራይስ ተጠይቀው ለአሁን መናገር የሚችሉት አምባሳደሩ የሚሄዱት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር እንደሆነ መሆኑን አመልክተዋል። በውይይቶቹ ዝርዝር ላይ መናገር የሚችሉት በማጠቃለያው እንደሆነና ዝርዝሩንም በፅሁፍ እንደሚያወጡ ገልፀዋል።

“ፀቡ ፈጥኖ እንዲወገድ፣ እየተካሄዱ ያሉት የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎችና ጥሰቶች እንዲቆሙ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲኖር፣ ከሰብዓዊው እንግልት ሌላ ለአፍሪካ ቀንድም ሰላምና ደኅንነት ሥጋት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭቱ መፍትኄ ላይ ድርድር እንዲካሄድ ለረዥም ጊዜ ስናንሳስብ ቆይተናል” ብለዋል ፕራይስ።

ልዩ ልዑኩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ አሁን ያለው ሁኔታ አመቺ መሆኑን የጠቆሙት ኔድ ፕራይስ ሁለቱም ወገኖች ውጊያ እንዲያቆሙና ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲቀርቡ ዕድል እንደሚሰጥ ባለሥልጣናቱ እንደሚያምኑም አመልክተዋል። አምባሳደር ፌልትማን ኢትዮጵያ ሲገቡም የውይይቱ ይዘት ይኸው እንደሚሆንም ገልፀዋል።

“ለግጭቱ መፍትኄ የለም ስንል፤ እንደመጀመሪያም፣ እንደመጨረሻም፣ እንደብቸኛ አማራጭም የምንደግፈው ዲፕሎማሲን እንደሆነ ስንናገር ቆይተናል” ብለዋል ቃል አቀባዩ። በመቀጠልም “የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ የሆነና በተፈፀሙ የጭካኔ አድራጎቶች ተጠያቂ የሆኑ የሚጠየቁበት ግልፅ የፍትኅ እርምጃዎችን ያካተተ ትዓማኒና ሁሉን አቃፊ ድርድር እንዲጀምር ጥሪያችንን በድጋሚ እናሰማለን” ብለዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply