ገና ተዋህዶ ኤክስፖ እንዳይደረግ ፍቃድ መከልከሉ ተነገረ።

ማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ጋር በመተባበር ከታህሳስ 11-27/2016 ዓ.ም በጃንሜዳ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ገና ተዋህዶ ኤክስፖ መሰረዙን ሰምተናል፡፡

የማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ባለቤት አቶ ኤፍሬም አደፍርስ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ቢሮ ፍቃድ ባለመስጠቱ ምክንያት የገናን ኤክስፖ ማካሄድ አልቻልንም ብለዋል፡፡

ይጀምራል ተብሎ ማስታወቂያ ከተነገረበት ቀን በስድስት ቀናት የዘገየው ኤክስፖው እስካሁን ፍቃድ የሚሰጠው አካል ባለማግኘቱ ማካሄድ እንዳልተቻለ ገልጿል።

የሚካሄድበት ቀን ከመድረሱ ቀደም ብሎ ወደ ጽህፈት ቤቱ ፍቃድ ለማግኘት ብዙ ተመላልሰናል ያሉት አዘጋጆቹ ዛሬ ነገ ስንባል ቀኑ በመድረሱ ምክንያት ነጋዴዎች ወደ ጃንሜዳ እንዲገቡ ብንፈቅድም በፖሊስ እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤቱ ቢሮ ሄደን ስንጠይቅ በደብዳቤ እናሳውቃችኋለን የሚል መልስ እንደተሰጣቸው የተናገሩት አቶ ኤፍሬም ፕሮግራሙ መካሄድ ካለበት ቀን እየገፋ ነው ብለዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱም ፍቃድ ለመስጠት ለምን እንዳልፈለገ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

ኤክስፖው ከቤተክርስቲያኗ ህጋዊ ፍቃድ የተሰጠው እና ለቤተክርስቲያኗ ገቢ ለማስገኘት ያቀደ ቢሆንም ማስታወቂያ የሰሙ ሸማቾችም ጃንሜዳ እየደረሱ እየተመለሱም ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠን የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ክፍልን ብንጠይቅም በዉሳኔዉ ላይ መረጃ እንደሌለዉ አስታወቋል፡፡

በለአለም አሰፋ
ታህሳስ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply