ገንዘብ ሚኒስቴር “ኤኤምኢኤ ፓዎር” ከተባለ ኩባንያ ጋር 600 ሚሊየን ዶላር ወጪ የሚደረግበት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለመገንባት ስምምነት ተፈራረመ

ሰኞ ህዳር 24 ቀን 2016(አዲስ ማለዳ) ገንዘብ ሚኒስቴር “ኤኤምኢኤ ፓዎር” ከተባለ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ኩባንያ ጋር 600 ሚሊየን ዶላር ወጪ የሚደረግበት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለመገንባት ስምምነት ተፈራርሟል።

የንፋስ ኃይል ማመንጫው ከምስራቅ አፍሪካ ግዝፉ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ የሚገነባው የንፋስ ኃይል 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ የተባለው ፕሮጀክት፣ በ18 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን በአገሪቱ የታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በዓመት 1 ነጥብ 22 ቴራ-ዋት የኤሌትሪክ ኃይል ማምረት እንደሚችል ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በግንባታ እና በቴክኒካዊ ስራዎች ሂደት 2 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል የተባለ ሲሆን፤ ይኸውም ለአካባቢው ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋጾ እንደሚያበረክትም ተገልጿል።

በሶማሌ ክልል የሚገነባውን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የሶስት አመታት ጥናት ቀድሞ መደረጉ ተመላክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply