ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ ያሳወቁት የሴት እና የአካል ጉዳተኞች አባላት ቁጥር የተጋነነ ነው ተባለ 

ዓርብ ሰኔ 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ማምሻውን ባወጠው መግለጫ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች በ2016 ዓ.ም ለቦርዱ ያሳወቁት የሴት እና የአካል ጉዳተኞች አባላት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የተጋጋነነ ነው ሲል አስታወቀ።

ፓርቲዎቹ በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ካቀረቧቸው ቁጥሮች አንፃር የሴት እና አካል ጉዳተኛ አባላት ቁጥር የተጋነነ በመሆኑ ማብራሪያ ተጠይቀዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጋቢት ወር ላይ ላቀረበላቸው የማብራሪያ ጥያቄ 10 ፓርቲዎች የተለያዩ ምላሾችን እንደሰጡ አስታውቆ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጨምሮ 11 ፓርቲዎች ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ቦርዱ መግለጫውን ካወጣበት ሰኔ 20 ጀምሮ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቀ ሲሆን ከጊዜ ገደቡ በኋላ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።

ምላሽ ያልሰጡት 11 ፓርቲዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ10 ሺህ እስከ 900 ሺህ የሚደርሱ ሴት እና አካል ጉዳተኛ አባላትን እንዳቀረቡ ተሰምቷል።

ብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ ራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት፣ ሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ የተጋነነ ቁጥር አቅርበዋል የተባሉ ፓርቲዎች ናቸው።

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዐብይ አህመድን ጨምሮ ምክትላቸው አደም ፋራህ በተለያየ ጊዜያት እንደተናገሩት የአባላቱ ቁጥር 14 ሚሊዮን ደርሷል ያሉ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ ግን በተለይ የሴቶችና አካል ጉዳተኞቹ መረጃዎች አላሳመኑኝም ሲል ውድቅ አድርጓል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply