ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሲ ወረዳ “ጋዋ ጋንታ” ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ውስጥ ጥር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦነግ
ሸኔ በተደረገው የዘር ፍጅት ሕይወታቸውን ላጡት የአማራ ብሄር ወገኖች “ያ ትውልድ ተቋም” የተሰማንን
ቅስም የሚሰብር ሀዘን ልንገልጽ እንወዳለን:: ድህነትና ጉስቁልና አልበቃ ብሎ ሕጻናትን፣ እናቶችንና ቤተሰብን
ሰብስቦ መፍጀት እጅጉን ልብ ያቆስላል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ አካሄዱን እየቀየረና አድማሱን እያሰፋ ለመጣው የዘር
ፍጅት አገዛዙ ለወራት አይቶ እንዳላየ ሆኖ ከቆየ በኋላ አሁን የአዞ እንባ ሲያነባ ይገርመናል:: ለአለፉት 50
ዓመታት ግድያና ለቅሶ ያልተለያት ሀገራችን በዚህ ሁለት ዓመት እየተፈጀ ያለው አማራ ጥፋቱ ቢባል ሀገሩን
ከመውደዱ ሌላ ከቶም አይኖርም:: ህወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ማግሥት ጀምሮ ያለማቋረጥ፣ ዛሬም
ለውጥ ላይ ነኝ ባለው አሻጋሪ አገዛዝ ጭምር በአማራው ህዝብ ላይ የደረሰውና ሰሞኑንም የተደረገው ዘግናኝ
የዘር ጭፍጨፋ ማንም ይፈጽመው ማን መንግሥት አስቀድሞ የዜጎቹንና መላ ሀገሪቷን ሰላምና ደህንነት
ሊያስጠብቅ አልቻለምና የጉዳዩ ቀጥተኛ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል እንጠቁማለን::
ኢትዮጵያ በጨቋኞችና በአምባገነኖች በመገዛት ሕዝቧ ፍዳውን ቢያይም ይኸኛው ግን ለየት ይላል::
ኢትዮጵያን የማይወድ፣ ህዝብን የማይወድ አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ ተንሠራፍቶ የዛሬ 28 ዓመት የዘራው የዘር
ፖለቲካ ዛሬ አንድን ዘር በማጨድ እየወቃው ይገኛል:: በአለፉት ሁለት ዓመታት ይህ ሥር የሰደደ የዘረኝነት
አገዛዝ ወራትን እየጠበቀ በተለያየ ሰበብ የጅምላ ፍጅት ሲካሄድ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው::
ያ ትውልድ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ አንድነትና ዋስትና ድምጹን በማሰማቱ የደረሰበት ጭፍጨፋ እስከዛሬ
ቢያንገበግበንም ታግሎና ታሪክ ሰርቶ ነውና እንኮራበታለን:: የዛሬው ግና መኝታቸውና ኩሽናቸው ከጭስ
ያልተላቀቀ፣ ማደሪያቸው ከከብቶች እስትንፋስ ያልተላቀቀ፣ ለብሰው በዋሉበት አዳራቸው የሆነ፣ የድህነት
ጫፉን በፍቅርና በወግ የሚረሱት ምስኪኖችን ማረድ፣ በፈንጂ ማጋየት፣ ቤት ንብረታቸውን ማቃጠል እጅጉን
ተሰምቶናል::
ያ ትውልድ ተቋም ከፖለቲካው ነጻ የሆነ ተቋም ቢሆንም ከተነሳንበት ዓላማ አንዱ ለ“ያ ትውልድ” ሰማዕታትና
ለፍትህ ዘብ መቆም ነውና መንግሥት በአለበት ሀገር ለእንዲህ ዓይነቱ ተደጋጋሚ የዘር ፍጅት ድምጽ
ለማሰማት የሞራል ብቃቱ አለንና የነዚህ ምስኪን ወገኖቻችን ደም ይፋረዳችሁ እንላለን:: በየጊዜው
እየተጨፈጨፉ ላሉ ወገኖች በተለይም የአማራው ህዝብ እልቂት ጊዜ ፍርድ እንደሚሰጥ አበክረን እየገለጽን
ለኢትዮጵያና ለሕዝባችን እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጠን እንላለን::
ኢትዮጵያ ከተደቀነባት የጥፋት አደጋ እግዚአብሔር ይጠብቃት!!!
ለንጹሐን ዜጎች እልቂት ጊዜ ፍርድ ይሰጣል!!!
ያ ትውልድ ተቋም
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም.
Email : [email protected]
website : http://www.yatewlid.com, http://www.yatewlid.org Facebook:- Yatewlid