ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀረበበት ክስ ላይ የዋስትና ብይን ለመስጠት በድጋሚ ተቀጠረ

አርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀረበበት ክስ ላይ የዋስትና ብይን ለመስጠት በድጋሚ ተቀጠረ።

በድጋሚ የተቀየረው በዋስትናው ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አንድ ዳኛ በመጉደላቸው ምክንያት ነው በድጋሚ የተቀጠረው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በተሟላ ዳኛ ዋስትናው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ፊታችን ሰኞ መቀጠሩን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሚሰራው ፍትህ መጽሔት ላይ በተለያዩ ቀናቶች የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥር በማውጣትና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል በተደራራቢ በ3 የወንጀል ክስ እንደተመሰረተበት ይታወሳል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ የተጠቀሰው አንቀጽ ከ5 ዓመት የማያንስ ጽኑ እስራትን የሚያስከትል ሲሆን፤ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት” የሚለው ወንጀልም በተመሳሳይ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ወንጀሉ ከባድ ከሆነ ቅጣቱ እስከ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊደርስ እንደሚችልም በህጉ ላይ ተቀምጧል።

“መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር” በሚለው ክስ ተመስገን ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ በቀላል እስራት አሊያም ወንጀሉ ከባድ ከሆነ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በወንጀል ህጉ ላይ ተደንግጓል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ክስ ቀርቦበት የሦስት ዓመት እስራት ከተበየነበት በኋላ፤ በዝዋይ ማረሚያ ቤት እስሩን ጨርሶ መውጣቱ ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply