ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስካሁን አለመፈታቱን ቤተሰቦቹ አስታወቁ

ቤተሰቦቹ ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን እንዲያከበር ጠይቀዋል

ማክሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ትናንት ሰኔ 27 ቀን 2014 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ቢወስንም እስካሁን ድረስ አለመፈታቱን ቤተሰቦቹ ተናገሩ።

የጋዜጠኛው ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ በማህበራዊ የትስስር ገፁ ባሰፈረው ፅሁፍ፤ ቤተሰቦቹ ለዋስትና የተጠየቀውን ብር አስይዘው የመፈቻ ወረቀቱን ይዘው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (ሦስተኛ) ቢሄዱም ፍቺውን የሚያስፈፅም አካል ባለመኖሩ ፖሊስ ጋዜጠኛ ተመስገንን ሳይፈታው እንዳሳደረው ገልጿል።

በዛሬው ዕለትም ቤተሰቦቹ ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (ሦስተኛ) ቢገኙም እስካሁኑ ሰዓት ድረስ አራት የሚሆኑ መርማሪ ፖሊሶች፤ የመርማሪ ፖሊስ ሀላፊዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግሯል።

በዚህም እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤቱ የወሰነው የፍቺ ጉዳይ መቋጫ አላገኘም ብሏል።

የሚመለከታቸው አካላት ህግ እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲከበር ጫና እንዲፈጥሩም ቤተሰቦቹ ጠይቀዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply