
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፌደራል ፖሊስን ሊከስ ነው። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ሀምሌ 7/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የ“ፍትሕ መጽሔት” ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዛሬ ሐምሌ 7/2015 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ ሲሆን፤ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ጠበቃ ቤተማሪያም አለማየሁ “ይህ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ታስሮ እንዲቀርብ በምን አግባብ ነው ትዕዛዝ የሰጠው?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ችሎቱም፣ ፈጽሞ ጋዜጠኛው “ታስሮ ይቀረብ” የሚል ትዕዛዝ አለመስጠቱን ገልጧል፡፡ ተመስገን ደሳለኝም በበኩሉ፣ ሰኔ 20/2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ወደ ቤቱ የመጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት “ትላንት ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስረን እንድናቀርብ ወስኗል፤” ብለው እንዳሰሩት አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም፣ ይህንን እስር የፈጸመው አካል ላይ ክስ ወይም አቤቱታ ማቀርብ ከፈለገ፣ በማመልከቻ እንዲያቀርብና ጉዳዩን መርምሮ እንደሚወስን በአጽንኦት መልሶለታል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ሕገ-ወጡን እስር በፈጸመው ፌደራል ፖሊስ ላይ ክስ ለማቅረብ ዝግጅት ጀምሯል፡፡ በሌላ በኩል፣ ዐቃቢ ሕግ “ጋዜጠኛው፣ መከላከል ያለበት የመከላከያን ምስጢሮች በማበክን እና የሠራዊቱን እንቅስቃሴ በማስተጓጎል ነው” ሲል ላቀረበው ይግባኝ፣ የጋዜጠኛው ጠበቆች ምላሻቸውን (ክርክራቸውን) በቃል እንዲያሰሙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱም “ለምን በቃል መከራከር ፈለጋችሁ?” ሲል ለሰነዘረው ጥያቄ፤ ደንብኛቸው የተከሰሰው በፖለቲካ ጉዳዮች ስለሆነ፣ ክርክሩ ለታዛቢዎች እና ጋዜጠኞች ክፍት ቢሆን ለእውነተኛ ፍትሕ አሰጣጥ የበለጠ እንደሚያመች ጠቅሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ፣ “በዚህ ወቅት መቅረጸ ድምጽ ስላሌለና የክርክሩን ጭብጥ በስክሪፕቶ ለመጻፍ ስለሚቸግር፤ ለችሎቱ በጽሑፍ አቅርባቸው፣ በእለቱ ለሚገኙ ተመልካቾች በንባብ እንድታሰሙ እንፈቅዳለን፤” ሲል ወስኗል፡፡ ክርክሩን ለማዳመጥ ለጥቅምት 5/2016 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ዘገባው የይድነቃቸው ከበደ ነው።
Source: Link to the Post