
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ተከራይቶ የሚሰራበት ስቱዲዮ ፀሃፊ መሰረት ታምሩ እና ወንድሙ አማኑኤል አስፋው ታሰሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የኢትዮ ሰላም የበይነ መረብ ሚዲያ መስራቹ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ከትናንት በስቲያ ፍርድ ቤት ቀርቦ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲወጣ መወሰኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ እስከ የካቲት 11/2015 ዓ/ም ድረስ ከእስር አልወጣም። ፖሊስ ፍ/ቤት በዋስ እንዲወጣ የፈቀደለትን ጋዜጠኛ ቴዎድሮስን ለፍተሻ በሚል በዛሬው እለት ተከራይቶ ወደሚሰራበት ስቱዲዮ መውሰዱን ሮሃ ቲቪ ከቤተሰቦቹ ሰምታለች። ታዲያ ወደ ስቱዲዮ ቴዎድሮስን ይዘው የሄዱት ፖሊሶች ወንድሙን አማኑኤል አስፋውንና ተከራይቶ የሚሰራበትን ስቱዲዮ ፀሃፊ መሰረት ታምሩን ማሰራቸው ታውቋል። ቴዎድሮስ ተከራይቶ የሚሰራበትን ስቱዲዮ የአከራይ ተከራይ ውል ቢያሳይም ፖሊስ የአከራዩን ፀሃፊና ወንድሙን መውሰዳቸውን ነው ቤተሰቦቹ የተናገሩት። ፖሊስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ችግር ጋር ተያይዞ ባሰረው በጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ላይ ከትናንት በስቲያ ብሄርን ከብሄር ማጋጨት እንዲሁም ከአልሸባብና ከኦነግ ሸኔ ጋር መገናኘት የሚል ክስ እንዳቀረበበት ይታወቃል። የቴዎድሮስ ጠበቆች በበኩላቸው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቱን ተጠቅሞ ትንታኔ የሰጠ መሆኑን በመግለፅ የፖሊስን ክስ ተቃውመዋል። ዘገባው የሮሃ ሚዲያ ነው።
Source: Link to the Post