ጌታቸው ረዳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ያሳልፈው ውሳኔ “ትክክለኛ” እርምጃ ነው አሉ 

ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ጌታቸው ረዳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዛሬው ውሳኔ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የተደረገ አንድ እርምጃ ነው አሉ።

አዲስ ማለዳ ከጌታቸው ረዳ ይፋዊ የኤክስ ገጽ እንደተመለከተችው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ይፋ የተደረገበትን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ በማያያዝ “የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሰላምን ለማጠናከር ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ አንድ እርምጃ የተራመደ ነው” በማለት ገልጸዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህ.ወ.ሓ.ት በድጋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ በሕጋዊነት እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅድለትን ‘የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ’ እንዲሻሻል ረቂቁን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስተላለፉን አዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የቀደመው አዋጅ ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የማያስችል በመሆኑ ይህን ለመቀየር ማሻሻያው እንዳስፈለገ ገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህ.ወ.ሓ.ት. በአሸባሪነት እንዲፈረጅ በሚያዚያ መጨረሻ 2013 ላይ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ሲሆን መጋቢት 15 ቀን 2015 ላይ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዝ ፓርላማው መወሰኑ አይዘነጋም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply