ግልፅ ደብዳቤ አሻራ ሚዲያ ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ. ም. ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲስ አበባ ጉዳዩ: ወ/ሮ መስከረም አበራ ክቡር ኮሚሽነር ቀን…

ግልፅ ደብዳቤ አሻራ ሚዲያ ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ. ም. ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲስ አበባ ጉዳዩ: ወ/ሮ መስከረም አበራ ክቡር ኮሚሽነር ቀን: ግንቦት 6 2015 ዓ.ም በቅድሚያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ጊዜዎን ወስደው በ24 ታኅሳስ 2015 የወ/ሮ መስከረም ህገ ወጥ እስርን አስመልክቶ ለጻፍነው ደብዳቤ ምላሽ በመስጥትዎ ምስጋናችንን ከፍ ያለ ነው። መምህርት፣ ፀኃፊና ጋዜጠኛ መስከረም አበራ በፈጠራ የሽብር ወንጀል ሚያዝያ 1 2015 ዓ.ም ለ3ኛ ጊዜ በአገዛዙ አካል ከቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለው፣ በሽብር ወንጀል ተከሰው ሚያዝያ 26 2015 ዓ.ም በፌዴራል በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ቀርበው ነበር። ፓሊስ በህግ አግባብ ባለው መንገድ በቂ ማስረጃ ቀደም ብሎ አሰባስቦ አንድን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይገባዋል። ለክስ የሚያበቃ በቂ ማስረጃ ቀደም ብሎ ሳያሰባስብ፣ ፓሊስ ፍርድ ቤት አንድን ተጠርጣሪ ለይስሙላ አቅርቦ የምርመራና የምስክር ማሰባሰቢያ ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ደግሞ ደጋግሞ በመጠየቅ ህዝቡ ህግ ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት እንዲያጣ እየተደረገ ነው ። በሚያዝያ 26 2015 ዓ. ም የወ/ሮ መስከረም አበራ የፍርድ ቤት ውሎ፣ ፓሊስ እንደተለመደውና እንደሚጠበቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ በፍርድ ቤት ተፈቅዶለታል። እነ ወ/ሮ መስከረም አበራን በፈጠራ ወንጀል እንዲታሰሩ ቀድሞውንም ትዕዛዝ የሰጡ ባለስልጣኖች፣ ከፍርዱ ሂደት አስቀድሞ በሚዲያ የወ/ሮ መስከረም የስልክ ልውውጥ ነው ያሉትን ለቀዋል። ይሄ ብዙ መሰረታዊ የህግ ጥያቄ ያስነሳል። ተጠለፈ የተባለው የስልክ ልውውጥ እውነት ይሁን በዘመኑ ቴክኖሎጂ የተቀነባበረ መሆኑ የማይታወቅ፣ እውነት እንኳን ቢሆን የግለሰቦችን ስልክ መጥለፍና በሚድያ መልቀቅ ህጋዊ አግባብ ስለሌለው በህግ እንደሚያስጠይቅ፣ የፍርድ ሂደቱን የሚያዛባ፣ ፍርድ ቤትን የሚንቅና ፍርድን ወደ ሚድያ የወሰደ፣ የአገዛዙ ህገ ወጥ አካሄድ ነው። በአጭሩ የመንግስት አካሄድ አንድን ተጠርጣሪ በተከሰሰበት ወንጀል ነጻ ወይም ጥፋተኛ ብሎ ሊወስን የሚችለው ፍርድ ቤት መሆኑን የሚጻረር መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው። ክቡር ኮሚሽነር ወ/ሮ መስከረም አበራ የፓለቲካ እስረኛ ናቸው። ብቸኛው ጥፋታቸው ደግሞ በተፈጥሮና በህግ የተሰጣቸውን ኃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በኃላፊነት መጠቀማቸው ነው።ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን በፈጠራ ወንጀል ከአገዛዙ የተለየ የፓለቲካ ዓመለካከት ያላቸው ነጻ ሰዎችን ማሰር አገዛዙ እንዲያቆም ጫና ሊደረግበት ይገባል። አገዛዙ ህግን የፓለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሳሪያ ማድረጉን ገፍቶበታል። ክቡር ኮሚሽነር ስለዚህ እርስዎና የሚመሩት መስሪያ ቤት የወ/ሮ መስከረም አበራን የፍርድ ሂደት በቅርብ እንዲከታተል፣ ፓለቲከኞች ህግን የፓለቲካ መሳሪያ በማድረግ ወ/ሮ መስከረም አበራ በህግ ስም ማገትና ማንገላታት እንዲያቆሙ እንዲያሳስቡ ከታላቅ አክብሮት ጋር እናሳስባለን። ከአክብሮት ጋር የመተከል ድጋፍ ኮሚቴ ለንደን

Source: Link to the Post

Leave a Reply