ግሎባል ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር 30 በመቶ ለቆጠቡ አባላቱ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በብድር አስረከበ።30 በመቶ እና ከዛ በላይ ለቆጠቡ አባሎቹ እስከ 5 ዓመት ተከፍሎ በሚጠናቀቅ ብድ…

ግሎባል ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር 30 በመቶ ለቆጠቡ አባላቱ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በብድር አስረከበ።

30 በመቶ እና ከዛ በላይ ለቆጠቡ አባሎቹ እስከ 5 ዓመት ተከፍሎ በሚጠናቀቅ ብድር ነው መኪኖቹን ያስረከበው።

የመኪኖቹ ዋጋ 2.8 ሚሊየን ብር ሲሆን፤በ30 በመቶ ቁጠባ ወይንም በ850ሺህ ብር ለ12 አባላት መኪኖቹን በዛሬው እለት አስረክቧል።

የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች የሆነው “ሆን ዞ” የኢትዮጵያ እና ምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ወኪል የሆነው ኢትዮፒካር ብራንድ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት እያቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

በዛሬው ዕለትም ለግሎባል ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር አባላት የኤሌክትሪክ መኪኖችን አስረክቧል።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሞላ ባዘዘው ማህበሩ ከተቋቋመበት ከዛሬ 8 ዓመት ጀምሮ ለስራ መነሻ፣ ለስራ ማስፋፊያ ፣ ለትምህርት ፣ ለጤና እንዲሁም ለሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የብድር አገልግሎት በዝቅተኛ ወለድ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት ለአባላቱ ከተሰጡት የኤሌክትሪክ መኪኖች በተጨማሪ ግሎባል ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ከኢትዮፒካር ብራንድ ጋር አባላቱ በብድር መኪና ማግኘት የሚችሉበትን ስምምነት ፈርሟል።

በባንክ የብድር አማራጭ እየቀረቡ የሚገኙት እነዚህ መኪኖች የፋብሪካ ዋስትና ያላቸው ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ድርጅቱ መኪኖቹን መቶ በመቶ በብድር ብቻ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮፒካር መስራች እና ባለቤት የሆኑት አቶ ሳሙኤል አዲስአለም ናቸው።

ማህበሩ ከዚህ ቀደም ከባንኮች ጋር በመተባበር ከአርባ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቹ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን ማስረከቡም ተገልጿል።

ዛሬ የማስጀመሪያ ፕሮግራም መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ከዚህ በኋላ በየወሩ ከ1መቶ እስከ 1መቶ 50 መኪኖችን ለአባላቱ እንደሚያስረክብ ተናግረዋል።

በ13 በመቶ ወለድ ብድሩ በ5 ዓመት ውስጥ ተጠናቆ የሚያልቅ ይሆናል።

ግሎባል ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ከ2ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፤ በአዋጅ ቁጥር 985/2009 የተቋቋመ የብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር ነው።

በእስከዳር ግርማ

ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply