ግብፅ ለሶማሊያ ያላትን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አሳወቀች፡፡

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ ጥያቄ ካቀረበች ከጎኗ ለመቆም ጣልቃ እንደምትገባ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ተናገሩ።

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በባሕር በር አጠቃቀም ዙሪያ የመግባባያ ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ሶማሊያ ተቃውሞ ያቀረበች ሲሆን፣ ግብፅም በተደጋጋሚ የሶማሊያን አቋም ደግፋ አስተያየት ስትሰጥ ቆይታለች።

የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከግብፅ መንግሥት በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ካይሮ በመጓዝ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ሁለቱ አገራት ከኢትዮጵያ አንጻር በጋራ እንሚቆሙ የተገለጸው።

ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ አገራቸው በሶማሊያም ሆነ በፀጥታዋ ላይ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንዲፈጠር እንደማትፈቅድ እና ለዚህም ግብፅ ጣልቃ እንድትገባ ከተጠየቀች ከሶማሊያ ጎን ትሰለፋለች ሲሉ ተናግረዋል።

አል-ሲሲ ይህንን ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረውን አስተያየት ከሰጡ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ብለዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ለምታገኘው የባሕር ጠረፍ፤ በምላሹ ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።

ይህ ታዲያ ሶማሊያን በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን፣ በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱን አጥብቃ ተቃውማለች።

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በቀጣናው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ወደ አሥመራ እና ካይሮ ጉዞዎችን አድርገዋል።

ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply