ግድባችንን በልበ ሙሉነት እንደጀመርነው በተባበረ ክንዳችን በላብና በጥረታችን ገንብተን እናጠናቅቃለን- የደቡብ ክልል መንግስት

ግድባችንን በልበ ሙሉነት እንደጀመርነው በተባበረ ክንዳችን በላብና በጥረታችን ገንብተን እናጠናቅቃለን- የደቡብ ክልል መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ከደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል ፡፡

የክልሉ መንግስት በመግለጫውም ግድባችንን በልበ ሙሉነት እንደጀመርነው በተባበረ ክንዳችን በላብና በጥረታችን ገንብተን እናጠናቅቃለን ሲል ገልጿል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ የሚያስቆመን አንዳችም ምድራዊ ሀይል የለምም ነው ያለው።

የክልላችን ብሎም የሀገራችን ህዝቦች የጋራ ጥረት የግድቡን ግንባታ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ነውም ብሏል፡፡

ህዝባችን የእለት ጉርስ ከሌለው ዜጋ ጀምሮ ሁሉም እንደየ አቅሙ ያለውን እያዋጣ ከዳር እስከ ዳር በአንድ ድምጽ ሆ ብሎ በመነሳት ለግድቡ ግንባታ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።

ይህ ሀገራዊ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የክልላችን ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለምም ብሏል በመግለጫው።

ይህ ህዝባዊ መነቃቃት የፈጠረው ቁጭት ነገ እንደሀገር ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጉዞ የሚያቃልል መሆኑን በመረዳት ነው ብሏል።

ወደ እድገትና ብልጽግና በሚደረግ ጉዞ መቸም ቢሆን የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናልም ነው ያለው።

ከሚገጥሙን ፈተናዎች ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት አንዱ ነው ያለው የክልሉ መንግስት በመግለጫው÷ለዚህ ትራምፕ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተናገሩት አንዱ ማሳያ ነው ብሏል በመግለጫው።

ይህም ንግግራቸው የሀገራችንን ህዝብ ያሳዘነ ተግባር ነው ሲል ገልጾታል ።

ይህንን ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ የክልሉ መንግሥት ሚናውን የሚወጣ ይሆናልም ነው ያለው።

ለዚህ ተግባር ደግሞ የክልሉ ህዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚሰነዘረውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ በመግለጫው መግለጹን ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

The post ግድባችንን በልበ ሙሉነት እንደጀመርነው በተባበረ ክንዳችን በላብና በጥረታችን ገንብተን እናጠናቅቃለን- የደቡብ ክልል መንግስት appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply