ሰሞኑን የትግሬ ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ አሰልጥኖ ጃዝ ባላቸው ቅልብ ነፍሰ ገዳዮቹ፣ በኦሮሞ እህት ወንድሞቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያና ማፈናቀል፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በጽኑ ያወግዛል። ይህ አንዱን ነገድ በሌላው ነገድ ላይ በማስነሳት፣ አንደኛው ሌላውን ከክልሌ ውጣ ማለት የወያኔ የሥልጣን ዘመን ማራዘሚያና ኢትዮጵያን የማፈራረሻ ስልቱ እንደሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምን ሁሉ ዐውቆ ፣ወያኔ ሆን ብሎ ከሚያጠምደው የራስ በራስ መጠፋፋት ተግባር ራሱን ሊቆጥብ ይገባል ብለን እናምናለን።
ይህ ሰሞኑን ወያኔ ሆን ብሎ በሶማሌና በኦሮሞ ነገዶች መካከል የለኮሰው ብጥብጥ ፣ ከገጠመው ሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ የሕዝቡን የትብብር እንቅስቃሴ ለማዳከምና ሕዝባዊ አመጹን በሚሻው መልኩ ለማጨናገፍ ፣ የትግሉን አቅጣጫ ለማሳትና የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ያጠመደው ወጥመድ መሆኑን በግራ በቀኙ ያሉ የሁለቱ ነገድ አባሎች ሊያስተውሉት ይገባል። የኦሮሞና የሶማሊያ ነጎዶች ዘላለማዊ ሲሆኑ፣ የትግሬ ወያኔ አገዛዝ ጊዜአዊ ነው። ጠፊና ተለዋጭ ነው። ኦሮሞና ሶማሌ ለዘመናት አብረው የኖሩትን ያህል ወደፊትም ተፈጥሮ በአንድ መልከዐምድር አቆራኝቷቸዋልና ማንም ሊለያያቸው አይችልም። ይህን ወያኔ አስቦና አቅዶ በሁለቱ ነገዶች መካካል ከራሱ ፍጡር «የሶማሊያ ክልል» ርዕሰ መስተዳድር ነኝ፣ ከሚለው ግለሰብ በስተኋላ ሆኖ፣በኦሮሞ እህት ወንድሞቻችን ላይ የወሰደው የግድያና የማፈናቀል ተግባር፣ እኛ ለራሳችን ነገድ ኅልውና እና መብት የምንታገል እና በእኛ ላይ በከፋ ሁኔታ ላለፉት 27 ዓመታት ሲፈጸምብን የኖርንና ያለን የዐማራው ልጆች፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በሌሎች ላይ ሲፈጸም ስናይ የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ ልንል አይቻለንም። በመሆኑም በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን ግድያ፣ ስቃይና ማፈናቀል በጥብቅ ከማውገዝ አልፈን፣ ኢትዮጵያ ማለት በውስጧ የሚኖሩ ነገድና ጎሳዎች አንድነት የፈጠሩት አገርና የነርሱ ማንነት መለያና መታወቂያ ናት፤ ይህ ማንነትና መታወቂያ ተጠናክሮና ዳብሮ ሊቀጥል ይገባል ከሚሉ ቡድኖችና ስብስቦች ጋር በመሆን፣ የወያኔን የመከፋፈል ሤራ ከማክሸፍ ማሻገር፣ ወያኔን ገፍትሮ ለመጣል ለሚደረገው ግብግብ፣የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው።
የዚህ ድምዳሜ መነሻ ምክንያት መገደል፣ መሰቃየት፣ መሰደ,ድና መፈናቀል ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ በፊልም፣ ወይም በታሪክ ሳይሆን፣ አስከፊነቱን እናት አባቶቻችን፣ እህት ወንድሞቻችን፣ አክስት አጎቶቻችን፣ አብሮአደግ ጓደኞቻችን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን እና የሥራ ባልደረቦቻችን፣ ከሁሉም በላይ ወደው ወይም መርጠው ሳይሆን፣ በተፈጥሮ ሕግ አማርኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ካደረጉ ወላጆች በመወለዳቸው ብቻ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በከፋ፣ በወለጋ፣ በኢሊባቡር፣ በሸዋ፤ በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም ወዘተ ይኖሩ በነበሩ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን እጅግ ዘግናኝ ግድያ፣ ሥቃይና ማፈናቀል፣ በካል ያየና፣ ሥቃዩና መሳደዱም ያለቆመ ስለሆነ፣ በእኛ ወገኖች ላይ የተፈጸመው ግፍ በሌሎች ላይ ሲፈጸም ስናይና ስንሰማ በእኛ ቁስል ላይ ጨው የመነስነስ ያህል ሆኖ ተሰምቶናል። በራሱ ላይ የተፈጸመ ግድያ፣ ሥቃይና መፈናቀል በሌሎችም ላይ ሲፈጸም እያየ ድርጊቱ ከማውገዝ ባሻገር፣ ለማስቆም ከተጠቂ ወገኖች ጎን ያልቆመ ቡድንና ስብስብ፣ በራሱም ወገኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ጥቃት ከዕውነት ይከላከላል ለማለት አያስደፍርም።
ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስናወሳ፣ የነገራችን መነሻና መድረሻ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መቸገርና መሰቃየት የሁሉም ኢትዮጵያ መቸገርና መሰቃየት መሆኑን ስናምንና ያ ክፉ ነገር በማንም ላይ እንዳይፈጸም ማድረግ የምንችለውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ ስንሆንና ይህንንም በተግባር መግለጽ ስንችል ነው። ለዚህም ዛሬ የትግሬ ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ፣ በዐማራውና በኦሮሞው ነገዶች ላይ ያነጣጠረውን ነጣጥሎ የመምታት፣ አንዱን በሌላው የማስመታት ሤራ ግብ ምን እንደሆነ አውቀን፣ ሤራውን ለማክሸፍ የወያኔ የጥቃት ዒላማ ከሆኑ ወገኖች ጎን በመቆም የወያኔን ዕድሜ ለማሳጠር መትጋት ይጠበቅብናል።
ወያኔ በሥልጣን የመቆያው ብቸኛ መንገድ፣ ነገድና ጎሣዎችን በመለያየት መሆኑን የሚከተለው የዘር ፖለቲካ፣ በቋንቋ ላይ የተመሠረተው «ፌደራላዊ አስተዳደር» እና ያነገበው የፀረ-ዐማራ አቋሙ በግልጽ ያስረዳሉ። ከሁሉም በላይ የወያኔ የአገዛዝ ዕድሜ መሠረቱ በዐማራውና በኦሮሞው ነገዶች መካካል የጥላቻ ግንብ በመገንባት እንደሆነ ሟቹ መለስ ዜናዊ «ዐማራው እና ኦሮሞው መልሰው ጋብቻ ከመሠረቱ፣ ያን ጊዜ ሕወሓት ያልቅላታል» ሲል የተናገረውና የአገዛዙን የግዛት ዘመን ለማራዘም በኦሮሞውና በዐማራው ነገዶች መካከል የልዩነት ዘርን ሲዘራ መኖሩን ማንም ይስተዋል አይባልም።
በዚህ ስሌት መሠረትም የኦሮሞና የዐማራ መጭ ትውልዶች ባንድ እንዳይቆሙ የሚያስችል የጥላቻ ግንብ «አኖሌ» የተባለ የተስፋዬ ገብረአብ የምናብ ድርሰት ሐውልት እንዲቆምለት ተደርጓል። ሐረርጌ፣ ወለጋ፣ ኢሉባቡር፣ ከፋ፣ አርሲ፣ ጎጃም መተክል፣ ለዘመናት ይኖሩ የነበሩ ዐማሮችን በገፍ ከመገደላቸውም በላይ፣ አገራችሁ አይደለም ውጡ ተብለው በፀሐይ ብርሃን እየታደኑ መባረራቸው ይታወቃል። ዐማራው በነዚህ አካባቢዎች በገፍ ሲገደልና ሲፈናቀል፣« የጨው ክምር ሲናድ፣ ብስል ያለቅሳል፣ ሞኝ ይስቃል» የሚሉት ዕውን ሆኖ፣ ሌሎች ወገኖች ለምን ? የሚል ድምፅ ከማሰማት ተቆጥበው፣ ከፊሎቹ የድርጊቱ ተሳታፊዎች ሲሆኑ፣ ከፊሎቹ ደግሞ ድርጊቱን ትክክል ነው የማለት ያህል ዝምታን የመረጡ እንደነበሩ ይታወሳል። እኛ ኢትዮጵያን እንደሚወድ ማናቸውም ዜጋ፣ ኢትዮጵያ ማለት በውስጧ ለዘመናት የኖሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ከ81 ያላነሱ ነገዶች የወል ቤት ናት ብለን የምናምን የዐማራ ልጆች፣ በኦሮሞ እህት ወንድሞቻችን ላይ ሆን ተብሎ እየተፈጸመ ያለ የዘር ማጽዳት እና የጅምላ ግድያ፣ሞቱ፣ ሥቃዩ፣ መፈናቀሉና መሰደዱ በእኛ ይብቃ! በማለት ከዕውነተኛ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ወንድሞቻችን ጎን በመቆም፣ ወያኔን እስከ ግሥ ማንግሡ ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል ጎን በመቆም፣ የበኩላችን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችን ስንገልጽ፣ የእህት ወንድሞቻችን ደም፣ ደመከልብ ሆኖ እንደማይቀር እርግጠኛ በመሆን ነው።
የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት
ቅጽ ፪ ቁጥር ፩ ቅዳሜ መስከረም ፮ ቀን ፪ሺ፲ዓ.ም.