ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትግራይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን አረጋገጡ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትግራይ ክልል በመቐለ አካባቢ የአየር ድብደባ መፈጸሙን አረጋገጡ። በአየር ኃይል አማካኝነት የተወሰደው እርምጃ በአካባቢው በነበረው የከባድ መሳሪያ ማስቀመጫ ላይ እና ሮኬቶች ላይ የተወሰደ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠቅሶ ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል። 

በአየር ኃይል እርምጃ መውደማቸው የተገለጸው ሮኬቶች እስከ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ መወንጨፍ የሚችሉ መሆናቸውን በዘገባው ተጠቅሷል። ዛሬ አርብ ማምሻውን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ፤ ሮኬቶች ብቻ ሳይሆኑ ሚሳኤሎችም በሕወሓት ኃይል ቁጥጥር ስር እንደነበሩ አመልክቷል። 

ሮኬቶቹ እና ሚሳኤሎቹ በ“ኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት” የተገዙ እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። “በሕወሓት ውስጥ የመሸገው ኃይል ስግብግብ ጁንታ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠሩት ኃይል፤ ሮኬቶቹን የመጠቀም ፍላጎት በማሳየቱ በአየር ድብደባ የማውደም እርምጃ ተወስዷል ተብሏል። 

እርምጃው መንግስታቸው በመጀመሪያው ዙር የመከላከል እቅድ ከያዛቸው ሶስት አላማዎች አንዱ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በሶስተኛነት ያነሱት እቅድ፤ የሕወሓት ኃይል “ዋና ዋና ትጥቆች፣ ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶችን በመጠቀም ጥፋት ማካሄድ እንደይችል አቅሙን ማዳከም” እንደነበር ጠቅሰው ይህም ሙሉ ለሙሉ መሳካቱን አብራርተዋል። 

የትግራይ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 26 ባወጣው መግለጫ የውጊያ ጀቶች በመቐለ አካባቢ ድብደባ መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር። በመቐለ የሚገኙ አንድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ የውጊያ ጀቶቹ የመቐለን ከተማ አቋርጠው ሲያልፉ የታዩት ትላንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ እንደነበር ተናግረዋል። 

የጀቶቹን ድምጽ የሰማው የከተማው ነዋሪ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመደናገጥ ወደ መንገዶች በመውጣት መመልከቱን እኚሁ ምንጭ አስረድተዋል። ጀቶቹ የአየር ድብደባ ፈጽመውበታል የተባለው ቦታ በመሶበ ሲሚንቶ ፋብሪካ አቅጣጫ የሚገኝ ቦታ እንደሆነ ሰምቼያለሁ ብለዋል። የትላንቱን ድብደባ ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች እስካሁን ድረስ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግልጽ መረጃ እንደሌለም ጠቁመዋል። (በተስፋለም ወልደየስ -ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትግራይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን አረጋገጡ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply