ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ አስታወቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመከላከያ ሰራዊትን ከፊት ሆኖ ለመምራት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ አስታወቁ። የወቅቱ ሁኔታ “ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻ ፍልሚያ የሚደረግበት” እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጊዜው “ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት” ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ መወሰናቸውን ያስታወቁት ትላንት ሰኞ ጥቅምት 13፤ 2014  ምሽት በጹሁፍ ባወጡት መግለጫ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ይፋ የተደረገው እርሳቸው የሚመሩት ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂዶ “የተለያዩ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ” ከተነገረ ከሰዓታት በኋላ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር አለሙ ስሜ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ገለጻ፤ የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ ሁሉም የፓርቲው አመራሮች ወደ ግንባር ተሰማርተው ውጊያዎችን ለመምራት መወሰናቸውን ተናግረዋል። ውሳኔውን ሁሉም አመራሮች ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርጉትም ጠቁመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በትላንቱ መግለጫቸው “ሁሉም ሰው ተባብሮ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋግጣል” ብለዋል። “ከዚህ በኋላ በሩቁ ተቀምጠን ተቺና አራሚ የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። መደረግ ያለበትን እኛው ራሳችን እናድርገው። ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የአመራር ክፍተት በተመለከተም በትላንቱ መግለጫቸው አንስተዋል። “የሚፈጠረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ ዐቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ ዐቅማቸው ይከውናሉ” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ አስታወቁ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply