ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአምስት ወር ዉስጥ ከ18 ሺህ በላይ የወንጀል መዛግብት ውሳኔ ሰጥቼያለሁ አለ፡፡

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣ 2013 ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአምስት ወር ዉስጥ ከ18 ሺህ በላይ የወንጀል መዛግብት ውሳኔ ሰጥቼያለሁ አለ፡፡ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን እንደገለጹት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ፣ የፍትህ ስርዓትን በማስፈን እና
ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ ረገድ ተቋሙ በርካታ ስራዎችን መስራት ችሏል ብለዋል፡፡ በዚሁም መሰረት በአምስት ወር አፈጻጸም ውስጥ በሁሉም የወንጀል ዓይነቶች በዐቃቤ ህግ እና በፖሊስ የጋራ ጥረት የምርመራ ስራቸው ተጠናቅቆ ለውሳኔ ከቀረቡ 19 ሺህ 536 መዛግብት መካከል በ18 ሺህ 817 መዛግብት ላይ በዐቃብያነ ሕግ የተለያዩ ውሳኔዎች እንደተሠጡ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በሁሉም የወንጀል ዓይነቶች ክርክር ከተደረገባቸው 31ሺህ 562 መዛግብት ውስጥ በምስክሮች እና ተከሳሾች አለመቅረብ ምክንያት 1ሺህ 213 መዛግብት መቋረጣቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ በቀጣይም እነኚህን የተቋረጡ መዛግብት መልሶ በማስከፈት ክርክሩ እንዲቀጥል ለማድረግ ተከሳሾች እና ምስክሮች ወደ ችሎት እንዲቀርቡ ከፖሊስ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ አቶ አወል አክለውም የወንጀል ክሶችን በተመለከተ በሁሉም አይነት ወንጀሎች እና የወንጀል ደረጃዎች ስልጣን ባላቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቀጥታ ክስ ቀርቦ ክርክር ከተደረገባቸው 4ሺህ 058 መዛግብት መካከል በ3ሺ 883 መዛግብት ላይ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠ ሲሆን 175ቱ ተከሳሾች በነጻ የተሰናበቱባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ቀላል የወንጀል ጉዳዮችን በዕርቅ በመጨረስ በህብረተሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብሎም ሁሉንም ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ከመውሰድ ይልቅ አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም በስምምነት እንዲጨርሱ በማደራደርና በማስማማት በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ 3 ሺህ 198 መዝገቦችን በእርቅ እንዲያልቁ ተደርጓል፡፡መረጃዉን ያገኘነዉ ከጠቅላይ አቃቤህግ ነዉ፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply