ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር ተነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቅርብ ጊዜ በፊት ባሰራጩት የትዊት መልዕክታቸው ከዩናትይድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ገለጹ፡፡ 

በውይይታችን “በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው የጋራ ወዳጅነትና በቀጠናው ባሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል” ያሉት ጠቅላይ ምኒስትሩ “ሁለታችንም ገንቢ በሆኑና በመከባበር ላይ በተመሰረተ ግንኙነት የጋራ እሴቶቻችን ለማጠንከር ተስማምተናል” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩልም ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው ግጭትና ሰላምና እርቅን ለማስፈን እንዲቻል ስለሚካሄደው ጥረት መነጋገራቸውን አስታውቋል፡፡  

በቅርብ ስለተፈቱ የፖለቲካ እስረኞችንም አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ ምስጋናቸው የገለጹ መሆናቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡ 

ሁለቱ መሪዎች ግጭቱን ለማቆም የተኩስ አቁም ስምምነትን ማፋጠን ስለሚቻልበት የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን በአፋጣኝ ማከናወን ስለሚቻልበት ሁኔታ መነጋገራቸውም ተመልክቷል፡፡ 

በግጭቱ ተጎጂ የሆኑትን ሰላማዊ ሰዎችና በአስቸኳይ አዋጁ የታሰሩ ሰዎችን አሰመልክቶ የተነጋገገሩ መሆኑም በመግለጫው ተገልጿል፡፡ 

ፕሬዚዳንት ባይደን በቅርቡ በመካሄድ ላይ ስላሉ የአየር ጥቃቶችና በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ስላለው ጉዳት ያሳሰባቸው መሆኑን መግለጻቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኛ መሆንዋንና ከአፍሪካ ህብረት ጋር የተጀመረው ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ 

ሁለቱም መሪዎች በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነትና ትብብር ለማጠንከር ባለው እድል ዙሪያ በመወያየት ለዚህም ተጫበጭ መሻሻሎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ መስማማታቸው በዋይት ሀውሱ መግለጫ ተመልክቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply