ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይም ሌሎቻችንም መዘንጋት የሌለብን … – ነፃነት ዘለቀ

ነፃነት ዘለቀ ([email protected])

በትናንትናው ምሽት የአማራው ቴሌቪዥን ያስተላለፈውን የወያኔውን ቡድን የስቃይ ሰለባዎች አሳዛኝ ታሪክ ተከታተልኩ፡፡ ለኔም ሆነ የወያኔን አገዛዝ በቅርብ ለምንከታተል ወገኖች ይህ ነገር አዲስ አይደለም፡፡ ከማዘንም አልፈን አልቅስንበታል፤ ሰሚ አላገኘንም እንጂ ደጋግመን ጽፈንበታል፤ የሰው ልጅ ይሠራዋል ተብሎ በማይገመተው በዚህ የዐረመኔዎች ድርጊት እስከማበድ የደረስንም አለን፡፡ ጉዳዩ  ይህ አካላዊና አእምሯዊ ስቃይ በኔ ወይ ባንተ መድረስ አለመድረሱ አይደለም፡፡ እንኳንስ ለአንተም ነፃነት ተብሎ በተከፈለ ስቃይና መስዋዕትነት በማንም የሰው ዘር ላይ በሚፈጸም መከራና እንግልት ማናቸውም የሰው ልጅ ሊሰማውና ኅሊናውን ሊጠዘጥዘው ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ የዘር ጥላቻን መሠረት አድርጎ በንጹሓን ዜጎች የሚፈጸምን ግፍና በደል ለመቃወም ሰው ሆኖ መገኘት ብቻውን ከበቂ በላይ ነው፡፡ አንዳንድ እንስሳት – ለምሣሌ እንደ አንበሣ ያሉ አስፈሪ እንስሳት – አንድ ሰው ብቻውን በጫካ ቢያገኙ አጅበውና ከሌሎች ሆዳም ጅቦች ከልለው ወደ ሰዎች መንደር ያስገባሉ፤ አንዳንድ አጥቢ እንስሳትም የሰውን ጨምሮ የሌሎች እንስሳትን ጭቅሎች እናቶቻቸው ረስተዋቸው በጫካ ውስጥ ሲያገኙ ልክ እንደራሳቸው ልጆች በመቁጠር እያጠቡ ያሳድጋሉ፤ እኚህን መሰል ብዙ ድንቅ ተዓምራትን በምናይባት ዓለማችን ውስጥ ወያኔን የመሰለ በሰው አምሣል የተከሰተ ዐውሬ ሲገጥመን ነጭ ጥቁር ሳንባባል የሰው ልጆች በአጠቃላይ አለመታደላችንና መዋረዳችን ጣርያ መንካቱን እንረዳለን፡፡ እንዲያው ለነገሩ ግን አያት ቅድመ አያቶቻችን ምን አጥፍተው ይሆን ይህን የመሰለ ጉድ እሚወርድብን? መጠናት አለበት፡፡ አለነገር እንዲህ አንሆንም፡፡ “ብድር በምድር” እንዲሉ ነውና ጥንታውያን ወገኖቻችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰውንና ፈጣሪን የሚያስቀይም አንዳች መጥፎ ሥራ ሳያስመዘግቡ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ እኚህኞቹም እያስቀመጡ ነው፡፡ እያስቀመጡ ያሉት ግን ስንት ሽህ ትውልድ ከፍሎ እንደሚጨርሰው አንድዬ ይወቅ፡፡ በዘመኔ ይህን የመሰለ ጉድ አያለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ ትንግርት ነው!

ሕወሓት ከበረሃ ጀምሮ በሚሠራው ግፍና በደል የሰው ልጆች ብቻ አይደሉም ሲሰቃዩ የኖሩትና አሁንም እየተሰቃዩ የሚኖሩት፡፡ ቃላትና ጽንሰ ሃሳቦችም ከሰው ልጆች ባልተናነሰ ሕይወትና ነፍስ ኖሯቸው እንደነሱ እንደሚሰማን ባናውቅ እንጂ ምናልባትም በበለጠ በስቃይ ፍዳቸውን ሲበሉ ታዝበናል፤ አሁንም ድረስ ይህ ስቃያቸው ጋብ አላለም፡፡  ሕወሓት ሲሉ ሰምቶ “ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ ሰላም፣ እኩልነት….” የሚሉ ወርቃማ ቃላትን በየንግግሩና በየማኒፌስቶው ያስገባል፡፡ እነዚህ ግዑዛን ቃላት እጅግ፣ እጅግ እጅግ ያሳዝኑኛል፡፡ በተጓዳኝም ተፈጥሯዊ ባሕርይው ሲያስገድደው በዚያው አንደበቱና ብዕሩ “ጨቋኟን የአማራ ብሔርና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከምድረ ገጽ ማጥፋት የሕወሓት ማዕከላዊ ዒላማ ነው” ይላል፡፡ ለምንም ዓይነት ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ህግ የማይገዛው “ወላድ አትይህ” ሕወሓት በዚህ ሸፋፋ ጠባዩና ምግባሩ ላለፉት 43 ዓመታት ለያዥ ለገራዥ እንዳስቸገረ አንዲት ታላቅ ሀገር ድራሹዋን አጠፋ፡፡ አሁን ደግሞ ቀኑ ሲደርስ ፈጣሪ አሰባትና ትንሣዔዋን ሊያሳየን ዳር ዳር እያለ ነው፡፡

በወያኔ ስለሚሰቃዩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ቃላትንም ካነሳሁ አይቀር በማታው የአማራ ቴሌቪዥን  ክትትሌ የታዘብኩትን አንድ ነገር ላስታውስ፡፡ በዝግጅቱ ስቃያቸውን እንዲናገሩ ዕድል የሚሰጣቸው የወያኔ የስቃይ ሰለባዎች ስማቸው ከግርጌ ሲጻፍ ከስማቸው ሥር “በይቅርታ ከእስር የተፈታ” የሚል መግለጫ አለው፡፡ ያን ሳነብ ነው በወያኔ የሚሰቃዩ ቃላት ትዝ ያሉኝ፡፡ ከሜዳ ተይዞ ወይም ከሥራ ቦታው ታፍሶ ወይም ከሞቀ ቤቱ ታፍኖ አለምንም ኃጢኣትና ወንጀል ለመስማት ሳይቀር ለሚዘገንን ስቃይ የተዳረገን ዜጋ `በይቅርታ ተለቀቀ` ብሎ የራስን ወንጀል ወደ ንጹሓን ማላከክ በጭራሽ ተገቢ አይደለም፡፡ የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችም ይህን ያሰቡበት አልመስለኝም፡፡ በበኩሌ እነዚህ ዜጎች ይህን እኔ የተሰማኝን ነገር ሲታዘቡ ሌላ ወንጀል እንደተሠራባቸው የሚቆጥሩት ይመስለኛል፡፡ በሰለጠነው ዓለም አንድ ሰው ባልሠራው ወንጀል ችግር ቢደርስበት ችግር ያደረሰበት ወገን ሙሉ ካሣ ከፍሎና ይቅርታ ጠይቆ የኅሊና ቁስሉን እንደሚያክመው ግልጽ ነው፡፡ እኛ ሀገር ውስጥ ግን መንግሥት የሚባለውን በሕዝብ ጫንቃ ላይ የሚዘፈዘፍ ወምበዴ ለመቃወምና ለመክሰስ ኃይልና ጉልበትም ሆነ ሥልጣን  ስለሌለን ተበድለን እንደበደልን፣ ተገፍተን እንደገፋን፣ ሳናጠፋ እንዳጠፋን፣ ተዘርፈን እንደዘረፍን፣ ተሰርቀን እንደሰረቅን፣ ተገድለን እንደገደልን …. እየተቆጠርን ድርብርብ ግፍና በደል እንድንሸከም እንገደዳለን፡፡ በአጭሩ ማለት የፈለግሁት “በይቅርታ የተፈቱ” የሚለው ነገር “ሌላ መንግሥታዊ ስህተትና ወንጀልም ነው” ነው፡፡ የይቅርታንና የምሕረትን ጽንሰ ሃሳቦች የመንግሥት አካላትና አባላት እንዲያውቁ ካልተደረገ ማንም በማንም ላይ በህግ ማስከበር ስም ያሻውን እያደረገ “ይቅርታና ምሕረት ተደርጎልሃል” ቢል ከቀደመው የባሰ ጥፋት ነው፡፡ እኔ ለምሣሌ ከመንገድ ተወስጄ ከታሰርኩና በስም ስህተት ወይም ያለመረጃና ማስረጃ እንደታሰርሁ ተገልጾኝ “በይቅርታ ተፈትተሃል፤ ዘወር በል አንይህ!” ብባል ይህ ድርጊት ስህተት ብቻ ሳይሆን ያሰረኝን ወገን ፍርድ ቤት የሚገትርና ትልቅ ቅጣት የሚያስጥል ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡ እነዚህ ወገኖቼ እየተፈጸመባቸው ያለው ነገር ከዚህ የተለዬ አይደለም፡፡ ስለዚህ በቋንቋ አጠቃቀማችን ላይ አስተውሎት እንደሚያስፈልገን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ጋዜጠኞች በተለይ ከዚህ ተሞክሮ ብዙ ልትማሩና ለወደፊቱ ልትጠነቀቁ ይገባል፡፡

ይልቁንስ በማታ የኢቲቪ ዜና እንደታዘብኩት ዶ/ር ዐቢይን አደነቅሁት፡፡ ወያኔ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስላባረራቸው ምሁራን በተነገረው ዜና ደንቆሮው የትምህርት ሚኒስቴራችን “ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሥራቸው መመለስ ይችላሉ” ብሎ መናገሩን የሰማው ጠ/ሚኒስትራችን “ይቅርታማ መጠየቅ ያለብን እኛው ነን” ማለቱን ስሰማ “እግዚአብሔር ይህን ልጅ የሰጠን ለበጎ ነው፤ ገና ብዙ ነገር እናይ ይሆናል…” ብዬ ተፅናናሁ፡፡ ከእግዚአብሔር የመጣ ያስታውቃል፡፡ አንድዬ ይጠብቀው፤ እርሱን መስለውና የርሱን እምነት የደገፉ መስለው በርሱ ስም ሊያምሱን ከሚቋምጡ የውስጥ አርበኞችና በደርግ አማርኛ ከበራዥ ከከላሾች ፈጣሪ ይጠብቀን፡፡ ለርሱ ያዘኑና ለውጡን የደገፉ ከሚመስሉ እስስቶች ፈጣሪ ሀገራችንን ይታደጋት፡፡ ከአስመሳዮች ይጠብቀን፡፡ አሜን አላችሁ?

በመሠረቱ የወያኔና የይቅርታ ዝምድና ሁልጊዜ እንደገረመኝ ይኖራል፡፡ ወያኔዎች ይቅርታ ማስባልን የሱስ ያህል ተጠምደውበታል፡፡ ምን እንደሚያገኙበት አላውቅም፡፡ ወንጀለኛ ሰው ራሱ በድሎ ተበዳይን ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ ያረካዋል ማለት ነው፡፡ የወያኔዎች ደግሞ ከሁሉ የባሰ ነው፡፡ ይቅርታ ማስባልን እንዴት እንደሚያመልኩበት ትዝ ሲለኝ እገረማለሁ፡፡

ወደሌላ ቁም ነገር ልዙር፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በያዘው የይቅርታና ምሕረት አካሄድ ላይ ትንሽ ቅሬታ አለኝ፡፡ በመጀመሪያ እነዚህ ሰዎች ይቅርታንና ምሕረትን የሚረዳ ተፈጥሮ የላቸውም፡፡ በጭንቅላታቸው ውስጥ ተሸክመውት የሚዞሩት ነጭ ጭቃ ከፍቅርና ከይቅርታ ጋር የሚገናኝ አንዳችም ነገር የለበትም፡፡ እነሱ የሚያውቁት መግደልንና መዝረፍን ብቻ ነው፡፡ እነሱ የሚያውቁት በለውንና ደምስሰውን ነው፡፡ ሥሪታቸውም አስተሳሰባቸው ከዶሮ ሲሆን ሆዳቸው ከጅብና ከዓሣማ ነው፡፡ ስለዚህ ለነሱ ይቅርታንና ምሕረትን ለማድረግ መሞከር መቀለጃ መሆን ነው፡፡ አይገባቸውምና – ማለቴ አይረዱትምና፡፡ አብዛኛዎቹ ወያኔዎች ሰው ሆነው ሳይጨርሱ ገና በእረኝነታቸው ዘመን ወደ ትግል በመግባታቸው ስለሰው ምንነትና ክብር የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ አእምሯቸው ለመብልና መጠጥ እንደሰለጠነ ለዕውቀትና ለጥበብ ግን ሳይታደል እንዲሁ አረጁ፤ ያሳዝናሉ፡፡ በዚያም ምክንያት ግደሉ ሲባሉ፣ ግረፉ ሲባሉ፣ ጥፍር ንቀሉ ሲባሉ፣ እንደፈለጋችሁ ተገናኙዋቸው ሲባሉ፣ … ከእሽ በስተቀር ለምንና እንዴትን ሳይጠይቁ  ደግመው የማያገኟን ወርቃማ ምድራዊ ጊዜያቸውን በከንቱ አቃጠሉ – ሰው ሳይሆኑ፡፡ ይህም በራሱ ትልቅ መረገም ነው፡፡ እኛም እነሱም ተረግመን መሆን አለብን፡፡

የይቅርታና ምሕረት እጅ ሲሰነዘር ደግሞ ይቅርታና ምሕረት አድራጊው ወገንም የነዚህን ጽንሰ ሃሳቦች ትርጉም በቅጡ መረዳት አለበት፡፡ ነገርን ለማብረድ ሲባል፣ ተወግዶ የማይወገድን ብቀላ ለማስወገድ በማሰብ ጽንሰ ሃሳቡን ለማይገነዘብ “ሰው” “ይቅርታ አድርጌልሃለሁ” ቢባል ራሱም ላይቀበለው ይችላል – አያውቀውምና፡፡ የደነቆረን ሰው እንዲሰማ ማድረግ ከፍተኛ ትግልን ይጠይቃል፤ እንዲያም ሆኖ ላይሳካም ይችላል፡፡ በወያኔ ደግሞ የሚሞከር አይደለም፡፡ ይቅርታን መዝገበ ቃላት በሚገልጣት መልኩ ወያኔዎች ከነመፈጠሯም አያውቁም፡፡ ይቅርታን የሚያውቅ እኮ ትልቅ ሰው ነው – በነገራችን ላይ፡፡ እንዲያውም ይቅርታ መጠየቅን እንደመሸነፍ ሊቆጥሩት ይችላሉ፡፡ ይችኛዋን አስቸጋሪ ዐረፍተ ነገር በፈለጋችሁት መንገድ ብትረዱዋት ግዴለኝም –  በገቢርም በተገብሮም፡፡

ለማን ነው ይቅርታና ምሕረት የሚደረገው? በምን አግባብ? ምን ጥፋት ላደረሰ?…

ወያኔዎች ይቅርታ አያስፈልጋቸውም ወደሚል አቋም ያስጠጋኝ ከጥፋት የሚመለሱ ኃይሎች እንዳልሆኑ መረዳቴ ነው፡፡ በመሠረቱ አንድን ወገን በይቅርታ ማዕቀፍ ውስጥ የምናስገባው ጥፋቱን አውቆና ተጸጽቶ ይቅር በሉኝ ሲልና ጥፋቱን ሲያቆም ነው፡፡ በጥፋቱ የቀጠለንና “የተሳሳተም ይሁን ያልተሳሳተ የምከተለው መንገድ ብቻ ነው የሚያዋጣኝ” ብሎ የቆረጠን መደዴ አለፍላጎቱ “ይቅርታ አድርገንልሃልና ከስህተት መንገድህ ውጣ” ማለት አሁንም ልድገመው በራሱ በይቅር ተባዩ ወገን ጭምር መሣቂያና መሣለቂያ የሚያደርግ የዋህነት ነው፡፡ ከመነሻው ወያኔዎች ለነሱ ይበልጥ የሚጠቅመውን ይቅርታ የሚንቁ ደነዞች ናቸው፡፡

ለነገሩ ሕወሓቶች ይቅርታውን ተቀበሉም አልተቀበሉም ከጥንት ጀምሮ እስካሁኒቷ ደቂቃ ድረስ እየሠሩት የሚገኙት ወንጀልና ሀገራዊ ጥፋትና ውድመት ከይቅርታ በላይ ነው፡፡ አንድን ሕዝብ ጠቅልሎ ማጥፋት (ቢያንስ በሃሳብ ደረጃና ከዚሁ ሕዝብ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረውን ደብዛውን ማሳጣት)፣ ንጹሓን ዜጎች ላይ በምናውቀው ሁኔታ ፍጹም ኢ-ሰብኣዊ ተግባራትን መፈጸም፣ የአንድን ሀገር የወል ሀብትና ንብረት እንዲሁም አንጡራ ገንዘብ በአንድ ጎሣ ቁጥጥር ሥር አውሎ በአንድ ዘር የበላይነት በተጠናና በተቀናጀ ሁኔታ ሀገርን መዝረፍ፣ መሬትንና ግዛትን ለባዕዳን መሸጥ፣ ወዘተ. በተራ ይቅርታ የሚታለፍ ከሆነ ፍርዱን ለታሪክ መተው ይቀላል፡፡ በሆነ ነገር ተገፋፍቶ ዛሬን እንደምንም ማታለል ይቻል ይሆናል፡፡ ትናንትንም እንደነገሩ መሸንገል ይቻል ይሆናል፡፡ የነገን የትውልድና የፈጣሪ መሪር ፍርድ ግን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ወያኔዎች እየሠሩት ያለው አጠቃላይ ግፍና በደል እነሱም በሚንቁት የይቅርታና ምሕረት ያልተመጣጠነ “ቅጣት”  ይካካሳል ብሎ ማመን በትንሹ ሞኝነት ነው፡፡ ራስህን በራስህ ተቃረንህ ባልባል የነዐቢይን ጥረት ግን ማድነቅ አለብን – ለጊዜው ያለን ብቸኛ ምርጫ እርሱ ነውና፡፡ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ ከነዚህ የመሬት ውስጠኛ ክፍል ድረስ ሰቅስቀው ከገቡ ምስጦችና ነቀዞች ለመገላገል ከዚህ ከይቅርታና ምሕረት በላይም ካለ ያን በጥንቃቄ መጠቀም ለጊዜው አዋጭ ሳይሆን አይቀርም – “ወደሽን ገጣቢት…” እንዲሉ ነውና፡፡ ዓለማችንን ያስደነገጡ በዓይታነቸው የመጀመሪያም የመጨረሻም የሆኑ በላዔ-ሰቦች ናቸው፡፡ በተንኮልና በሸር እንዲሁም በክፋት ሥራ ሰይጣንን ሳይቀር በእጅጉ የሚያስከነዱ የጨለማው ግዛት አበጋዞች ናቸው – እውነቴን ነው – ሰይጣን ለነሱ እጁን ሰጥቷል – “አህያ በወለደች ታርፋለች”ና የኢትዮጵያን ጉዳይ ለነሱ አስተላልፎ እርሱ አሁን ዕረፍት ላይ ይመስለኛል፡፡ ስለወያኔ ክፋት ተናግሮ መጨረስ አይቻልም፡፡

የሰውን የዘር ፍሬ አኮላሽቶ፣ በሰው አካላዊና አእምሯዊ ሕይወት ላይ በግፍ ተጫውቶ፣ በሰው ደምና አጥንት ዋኝቶ፣ ሰውን ከነነፍሱ በመቅበር በሚገኝ አጋንንታዊ የደስታ ስካር ተዝናንቶ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የራስን ነገድ አባላት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ፖለቲካዊ ሥልጣን ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ ሌሎችን ለማስፈራራት በታቀደ ሁኔታ ይህን ሁሉ ወንጀል በሀገርና በሕዝብ ላይ ፈጽሞ “ይቅርታ አድርገንላችኋል” በሚል አስተማሪነት የሌለው “ርህራሄ” እነዚህን ጉዶች መልቀቅ “ጨዋታው ፈረሰ፣ ዳቦው ተገመሰ” ዓይነት የሕጻናት የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡ ይልቁንስ ለማይቀረው ጦርነት ተዘጋጁ! ወያኔ ካለጦርነት ከለቀቀች ከምላሴ ፀጉር ይነቀል፡፡ እኛ የምናውቅላቸውንም እነሱ ብቻ የሚያውቁትንም ይህን ሁሉ የወንጀል ዶፍ በሀገርና በሕዝብ ላይ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ዘመን ካዘነቡ በኋላ እንዲሁ በሰላም ይለቁናል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የፈጣሪ ልዩ ተዓምር ካልታከለበት በስተቀር በሰላም ይተውናል ማለት በተለመደው አገላለጽ ከእባብ ዕንቁላል ዕርግብ ይፈለፈላል ብሎ እንደመጠበቅ ነው፡፡ አይሆንም፡፡ 

ለማንኛውም መሆን ያለበት – መሆን ካለበት – ያጠፉና ያላጠፉ ይለዩ፡፡ የጥፋታቸው ዓይነትና መጠንም ይለይ፡፡ መልካም ያደረጉ ይመስገኑ፤ ይወደሱ፤ ይሾሙ፣ ይሸለሙ፡፡ ያጠፉ ደግሞ እንደጥፋታቸው መጠን ከመጠነኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ጀምሮ ሞት በሌለበት የረጂም ዓመታት እሥራት ወደ ማረሚያ ቤት ይግቡና የሠሩትን በደል ይረዱ፡፡ በሩዋንዳም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ውስጥ የተደረገው እንደዚህ ነው፡፡ በወንድሙ ብልት የውኃ ኮዳ ያንጠለጠለ፣ በእህቱ ብልት ቃሪያና ሚጥሚጣ የጨመረ፣ ወንድሙን በጨለማ ቤት ዘግቶ በርሀብና በወፌ ላላ የገደለ፣ ወንድምና እህቶቹ እንዳይራቡ(ዘራቸውን እንዳይቀጥሉ) በመርፌና በዱላ ቅጥቀጣ ያመከነ፣ በዘር ጥላቻ ተመርዞ ሁለት ትውልዶችን አሳድዶ የጨረሰ…. እንዲሁ በይቅርታ መልቀቅ ማለት ወንጀልን ከማበረታታት አይተናነስም፤ የይቅርታና ምሕረትንም ትርጉም አለመረዳት ነው – ኢትዮጵያውያን ከትንኝ የሚበልጥ ዋጋ እንዳላቸው ወንጀለኞች ማወቅ ካልቻሉ እንዴትምና መቼም ሊማሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ቀልዶች ሲቀለዱ ወዝ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ገና ለገና ሁሉም ፍላፃዎችና ቀስቶች በወያኔ እጅ ናቸው በሚል ይህን ያህል ወርደን ለገዳዮች የማይገባ ክብር መስጠት እነሱ ራሳቸውና ሌላው ዓለምም የፍርሀትንና የትግስትን ወሰን በማይለየው የይቅርታና ምሕረት ቸርነታችን እንዲታዘቡን ማድረግ ነው፡፡ ለነገሩ እኛ በይቅርታና ምሕረት ስም የፈለግነውን ብናደርግም የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀረው የሰማይና የምድር ንጉሥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጊዜውን ጠብቆ ለሁሉም እንደዬምግባሩ መክፈሉ አይቀርም፡፡ በሠፈሩት ቁና መሠፈር ዛሬ ሳይሆን ጥንት ነውና የተጀመረው፡፡

ላሰምርበት የምፈልገው ነገር ደግሞ አለ፡፡ “እኛም እንደነሱ እንጨክን” እያልኩ እንዳልሆነ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ – በሐሙራቢ ህግ እምብዝም አላምንም፡፡ የምለው ያለሁት – ቆንጆ አማርኛ – የምለው ያለሁት ይህን ሁሉ ለሰማይ ለምድር የሚዘገንን ወንጀል የፈጸመን ሰው አንድም ሳትቆነጥጠው “የዘረፍከውን ሀብት ይዘህ ከሠራኻው ወንጀል ጋር በሰፊው ሕዝብ መሀል እየተዝናናህ ተንሸራሸር” እንደማለት ነውና ክርስቶስ እንኳን ያላደረገውን ምሕረት ለማድረግ አንሞክር ነው (ክርስቶስ በይሁዳ ላይ ያሳለፈውን ከባድ ውሳኔ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት)፡፡ ይህ ዓይነቱ የተምቦረቀቀ የምሕረት ዕቅፍ ደግሞ የአሁኖቹን ወንጀለኞችም፣ የወደፊት ወንጀለኛንም አያስተምርም፡፡ ማንም እየተነሣ በሎሚ ተራ ተራ በሕዝብና በሀገር ላይ ጥሬ ብስናቱን እንዲለቅ ምክንያት ይሆናል፡፡ “እነእገሌ ምን ሆኑ?!” በሚል ወንጀለኝነትንና ዋልጌነትን ይበልጥ ያበረታታል፡፡ ስለዚህ እነሱ የፈጸሙትን ያህል ሳይሆን መጠነኛ ቅጣት ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የዘረፉ ከዘረፉት የተወሰነውን ለሀገር ይመልሱ፤ የገደሉና ያሰቃዩ ቢያንስ በተወሰነ እሥራት ይቀጡ – ከማንቂያ ትምህርት ጎን ለጎን፡፡ ዝም ብሎ መልቀቅ ግን አንድም ፍርሀት ነው አለዚያም ጉልበት ያለውና ቀን የሰጠው ሁሉ እየተነሣ በሕዝብና ሀገር ላይ የፈለገውን እንዲያደርግ ህጋዊ ፈቃድ እንደመስጠት ነው፡፡ እኔ እንዲህ አልኩ፡፡ እርስዎስ?

Leave a Reply