ጥንቃቄ ለቲቢ በሽታ ያሻዋል ተባለ።

በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ 10.6ሚሊዮን ህዝብ በቲቢ በሽታ ተጠቂ ይሆናል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ  በየአመቱ 1.3 ሚሊዮን ህዝብ ይሞታል ተብሏል ።

የቲቢ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷናት።

በየአመቱ በኢትዮጵያ 156 ሺህ ህዝብ እንደ አዲሲ በቲቢ ይያዛል ተብሏል ።

በአመት ከ100ሺህ ህዝብ 17 ዜጎች በዚህ ህመም ህይወታቸው እንደ ሚያልፍም  ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን  ኢትዮ ኤፍ ኤም የቲቢ በሽታ ተመራማሪና ግሎባል ፈንድ ግራንት አማካሪ የሆኑትን አቶ ፋሲል ፀጋዬን  ስለበሽታው ምንነት ጠይቋቸዋል ።

አቶ ፋሲል ፀጋዬን ቲቢ  ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ነው ብለዋል፡፡

የቲቢ በሽታ ምንድን ነው?

ቲቢ ተላላፊ በሽታ ሲሆን  በባህሪው ቀስ በቀስ እያለ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ድንገተኛና አጣዳፊ ከሚባሉት የበሽታ ዓይነቶች ክፍል የሚመደብ አይደለም፡፡ የቲቢ በሽታ መንስኤም በዓይን የማይታይ ረቂቅ ተህዋስ ወይም ጀርም  ነው፡፡

የቲቢ በሽታ ሥርጭትና ተጽዕኖዎች፡

የቲቢ በሽታ ዛሬም የዓለም ሕዝቦች የጤና ችግር ሲሆን ኢትዮጵያም ቲቢ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሁም መድኃኒቶችን የተላመደ ቲቢ በከፍተኛ ሁኔታ ተሠራጭቶ ከሚገኝባቸው የዓለም አገሮች ውስጥ አንዷ ናት ብለውናል፡፡

ዚህም የተነሳ በሽታው የሚያስከትለው ሕመም፣ ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም ማኅሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ሲሉ አብራርተዋል ፡፡

ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሚሆኑት፡

 • ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት፣
 • አረጋዊያን፣
  -በኤች. አይ. ቪ. የተያዙ ሰዎች እንዲሁም
 • በአክታ ምርመራ የቲቢ በሽታ አምጪ ተሕዋስ ከተገኘባቸው ሕሙማን ጋር አብረው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡

ለበሽታው መስፋፋት የሚያመቹ ሁኔታዎች፡-

ለበሽታው መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ከሚፈጥሩ ነገሮች፡

 • በቂና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት፣
 • በቂ የአየር ዝውውር በሌላቸው ክፍሎች ውስጥ ተፋፍጎ መኖር፣
 • ሰውነት በተፈጥሮ ያለውን በሽታን የመከላከል አቅም በማዳከም ለሌላ ተደራቢ በሽታ የሚዳርጉ እንደ ኤች. አይ. ቪ./ኤድስ፣ ስኳርና ካንሰር የመሳሰሉት በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የቲቢ በሽታ መተላለፊያ መንገዶች

 • የቲቢ በሽታ በዋናነት የሚተላለፈው በሳንባ ቲቢ የተጠቃና ሕክምና ያልወሰደ በተለይም በአክታ ፣  በሳል፣ በማስነጠስ በሺታው በቀላሉ ይተላለፋል ብለዋል አቶ ፋሲል።

የበሽታው የማይተላለፍቸው መንገዶች?

 • በመጨባበጥ፣
 • አልባሳትን በጋራ በመጠቀም፣
 • መመገቢያና ማብሰያ የቤት ዕቃዎ በጋራ  ሰዎች ቢጠቀሙ በሺታው አይተላለፍም ብለውናል።

የቲቢ በሽታ ዓይነቶች

ቲቢ ሰማኒያ ከመቶ የሚሆነው የሚያጠቃው ሳንባን ቢሆንም ሌሎችንም የሰውነት ክፍሎችን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ስለሆነም በሽታው የሚጠቃውን አካል መነሻ በማድረግ የሳንባ ቲቢ እና ከሳንባ ውጭ የሆነ የቲቢ በሽታ በመባል ለሁለት ይከፈላል፡፡

የቲቢ በሽታ ምልክቶች

 1. የበሽታው ዋና ምልክት ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የዘለቀ ሳልና ሳሉ አክታ ያለውና ደም የቀላቀለ ወይም ያልቀላቀለ ወይም ደረቅ ሊሆን ይችላል፡፡

በተጨማሪ በደረት አካባቢ የውጋት ስሜት፣መጠነኛ የሆነ ትኩሳት፣ ሌሊት በመኝታ ጊዜ ማላብ፣ የክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና የሰውነት መድከም የመሳሰሉ ናቸው ይላሉ ባለሙያው ።

የቲቢ በሽታ ምርመራ

በታማሚው ላይ በሚታዩ የሕመም ምልክቶች፣ ከሕመምተኛው አክታ ወይም ከተጠቃው ከሳንባ ውጪ ከሆነው አካል ከሚወሰድ ፈሳሽ በላቦራቶሪ ምርመራ በማድረግ ነው ተብሏል ፡፡

የቲቢ በሽታ ሕክምና

የቲቢ መድኃኒቶች በዋጋ ደረጃ ውድ በመሆኑ
የቲቢ በሽታ ምርመራም ሆነ ሕክምና በሚደረግበት በመንግሥታዊና በተፈቀደላቸው የግል ጤና ተቋማት በነፃ ህክምና ይሰጣል ።

የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር

ህመምተኞች የታዘዘላቸውን መድኃኒቶችን ባለማቋረጥ መጠቀም፣  ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሲስሉም ሆነ ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫዋን በጨርቅ በመሸፈን የበሽታው አምጪ ተህዋስያን እንዳይሠራጩ በማድረግ መቆጣጠር እንደሚቻል አቶ ፋሲል ተናግረዋል ።

በተጨማሪም አክታን በየቦታው አለመትፋት፣የቤተሰብ አባላትን፣ ሌሎች የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ጉረቤቶችንና የሥራ ባልደረቦችን ሁሉ እንዲመረመሩ ማድረግ፣የመኝታ ቤት መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖርና የፀሐይ ብርሃንም እንዲገባ ማድረግ፤ በተቻለ መጠን ገንቢና ተመጣጣኝ የሆነ ምግብ መመገብ፣ሲጋራ ከማጨስና ከአልኮል  መጠጦች መራቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

*በመጨረሻም በዚህ ህክም የተያዘ ሰው ተገቢውን ህክምና በመውሰድ መዳን የሚቻል የበሽታ አይነት በመሆኑ ከሁለት እስከ ሥስት ሳምንት አንድ ሰው ሳል ሲኖርበት ወደህክምና ተቋማት በማምራት መታየት ይኖርበታል ተብሏል ።

ልዑል ወልዴ

ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply