ጦርነት ተቃዋሚ ሰልፎች በበርሊንና በዴንቨር

https://gdb.voanews.com/FEBF3B28-8905-4F49-AABE-CE77B4427135_cx0_cy0_cw98_w800_h450.jpg

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆም ግፊት እንዲደረግ የጠየቁ የትግራይ ተወላጆች ማኅበረሰቦች አባላት ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥም ኮሎራዶዋ ዴንቨር ከተማ ላይ ትናንት ሰልፎች አካሄደዋል።

ፍራንክፈርት የሚገኙት የትግራይ ተወላጆች ማኅበረሰቦች ጥምረት ሊቀመንበርና የሰልፉ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ግርማይ በርኸ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል በሰልፉ ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የተጓዙት የሰልፉ ተሣታፊዎች ጥያቄዎቻቸውን ለቻንስለር አንጌላ መርከል ቢሮ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የዴንቨር ኮሎራዶ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሂሩት ሃጎስም ትናንት ከሺህ በላይ እንደሚሆኑ የገለጿቸው የትግራይ ተወላጆች በዴንቨር ከተማ ካፒቶል ሂል አካባቢ ሰልፍ ማድረጋቸውንና ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የአየር ድብደባውም እንዲቆም፣ የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎቶች እንዲከፈቱ መጠየቃቸውን ተናግረዋል። “ዋናው ጥያቄአችን ጦርነት እንደማንፈልግ እንዲታወቅልን ነው” ብለዋል።

ፌደራሉ መንግሥት “በተወሰኑ የህወሓት ባለሥልጣናት ላይ እየተካሄደ ያለ ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ” ብሎ የሚጠራው ሲሆን የህወሓት ባለሥልጣናት ግን “በትግራይ ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው” ይላል።

ከዶ/ር ግርማይ በርኸና ከወ/ሮ ሂሩት ሃጎስ ጋር የተደረጉትን ቃለምልልሶች ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply