ፀሐይ ባንክ ሐምሌ 16 ቀን 2014 በይፋ ሥራ ይጀምራል

ሐምሌ 14 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ፀሐይ ባንክ በ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የተፈረመና በ734 ሚሊዮን ብር በሥራ ላይ በዋለ ካፒታል ተቋቁሞ <ፀሐይ ባንክ ለሁሉ> በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሐምሌ 16 ቀን 2014 በይፋ ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

ባንኩ ዝቅተኛ የአክሲዮን ግዢውን ከብር 100 ሺህ በመጀመር፣ በ373 ባለአክሲዮኖች ባንክን ለመስረት የሚያስችለውን ካፒታል በማሰባሰብና የመስራች ጉባኤውን የካቲት 11 ቀን 2013 በሸራተን አዲስ ሆቴል በማካሄድ፤ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀሉን የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ መስፍን ተናግረዋል፡፡

የባንኩ ዓላማ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ብቻ ሳይሆን፤ በፋይናንስ ዘርፉ በቂ ትኩረት ያላገኙትን የጥቃቅንና አነስተኛ፣ የግብርናውን ዘርፍ፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን እንዲሁም አዋጭ ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎችና ሥራ ፈጣሪዎች ተደራሽ መሆን ነው ያሉት፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ በዚህም ‹ለሁሉም የሆነ ባንክ> እንዲሆን የአገልጋይነትን ዕሴትን ተላብሶ ጉዞውን መጀመሩን ገልጸዋል።

ፀሐይ ባንክ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን በማዘን፤ ዘመኑን የዋጀ “ቴሚኖስ ትራንዛክት አር 21” የለቀቀውን የኮር ባንኪንግ ሲስተምን በመላበስ፤ ደንበኛውን የባንክ አልግሎት እና ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን እንዲሁም፤ የቢፒሲ ካምፓኒ ምርት የሆነውን ስማርት ቪስታ በመጠቀም አጠቃላይ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ይዞ መቅረቡም ተገልጿል።

ፀሐይ ባንክ ወደ ገበያ ሲገባ ሁሉን አቀፍ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ሲሆን፤ የሕብረተሰቡን የዕለት ከዕለት ህይወት ለለወጥ ተግቶ የሚሰራ ባንክ ይሆናል ያሉት ደግሞ፤ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ታዬ ዲበኩሉ ሲሆኑ፤ በተለይም የተሻሻሉ አሰራሮችን ይዞ በማቅረብ በህብረተሰቡ የኑሮ መሻሻልና እድገት ላይ የበኩሉን ሚና ለመጫወት በትጋት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በባንኩ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ዕለት 30 ቅርንጫፎች የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ሲሆን፤ በቅርብ ቀንም ባንኩ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ50 በላይ የሚያሳድግ ይሆናል ተብሏል፡፡

እንዲሁም በአንድ ዓመት ውስጥ 100 ቅርንጫፎችን በኹሉም የአገራች አካባቢዎች ለክፈት የሚያስችለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተነግሯል፡፡

ባንኩ የራሱን ብራንድ (መለያ) በዛሬው ዕለት ያስተዋወቀ ሲሆን፤ እንዲሁም በታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ቴድሮስ መኮንን (ቴዲ ማክ) የተዘጋጀው የህብረ ዝማሬም በይፉ አስተዋውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply