“ፈተና አቋርጠው ለወጡ ተማሪዎች ምንም አይነት እድል አይሰጥም” የሚለው የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ዳግም እንዲታይ ተጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም…

“ፈተና አቋርጠው ለወጡ ተማሪዎች ምንም አይነት እድል አይሰጥም” የሚለው የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ዳግም እንዲታይ ተጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የትምህርት ሚኒስቴር ጥቅምት 2/2015 ከ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጋር በተያያዘ በሰጠው መግለጫ በአማራ ክልል በመቅደላ አምባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ባህርዳር እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች 12 ሺህ 787 ተማሪዎች ጊቢውን ለቀው መውጣታቸውን አስታውቋል። “አቋርጠው ለወጡ ምንም አይነት እድል አይሰጥም” የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ከተለያዩ አካባቢዎች ቅሬታዎች እየደረሱት ነው። ሚኒስትሩ ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው ፈተና አቋርጠው ለወጡ ተማሪዎች ሚኒስቴሩ ምንም አይነት እድል እንደማይሰጥ አሳውቋል። ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ “ፈተናው በተጀመረበት ወቅት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የደረሰው አደጋ እና በአማራ ክልል በመቅደላ አምባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ባህርዳር እና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች አንፈተንም በማለት 12 ሺህ 787 ተማሪዎች ጊቢውን ለቀው መውጥተዋል ” ሲል አሳውቋል። ትምህርት ሚኒስቴር በመግለጫው ፤ ” ከሌሎቹ በተለየ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ሃይል በተቀላቀለበት መልኩ በደረሰ ግርግር የአንድ (1) ተማሪ ህይወት ሲያልፍ በፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ገልጧል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የአማራ አካባቢዎች በተለይም ከመቅደላ አምባ፣ ከደብረ ማርቆስ፣ ከባህርዳር እና ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) የደረሰው ቅሬታ እንዳመለከተው በአንዳንዶች ግቢዎች በፈተና ሂደቱ፣ በአፈታተኑ፣ በፈታኞች እና በጸጥታ አካላት ላይ ችግር እንደነበር አውስተዋል። ከዚህ በተጨማሪም:_ 1) በኦሮሚያ ክልል ፈተናው ወጥቶ ተጭበርብሯል፤ በማህበራዊ ሚዲያ ተመልክተናል። 2) ወደ ኦሮሚያ ክልል ፈተና ለመስጠት ከሄዱ መምህራን መካከል ኃላፊነቱን አንወስድም በመባላቸው የተመለሱ አሉ። 3) የጸጥታ አካላትና ፈታኞች ያልተፈለገ ወከባ ፈጥረውብናል የሚሉ እና መሰል ቅሬታዎችን በማንሳት እንዲስተካከል ጠይቀዋል። በጥቅሉ በአንዳንድ ተማሪዎች የታዬው ክፍተት እንዳለ ሆኖ ብዙዎች በሁኔታዎች ጫና እና በመንግስት ድክመት ጭምር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ “ፈተና አቋርጠው ለወጡ ተማሪዎች ምንም አይነት እድል አይሰጥም” የሚለውን ውሳኔ ዳግም እንዲያጤነው እና እንዲያስተካክል ከአሚማ ጋር ቆይታ ባደረጉ ተማሪዎችና ወላጆች ተጠይቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply