ፋሲካ (በዓለ ትንሣኤ)

ፋሲካ (በዓለ ትንሣኤ) በዘመነ ሐዲስ የክርስቶስን ትንሣኤ የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ ይህ በዓል ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፤ ከውርደት ወደ ክብር፤ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነጻነት፤ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ ሕይወት የተሻገርንበት ነው በሚል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት ነው የሚከበረው።

‹ፋሲካ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ፌሳሕ›፤ በጽርዕ (በግሪክ) ‹ስኻ› እንደሚባል መንፈሳዊ መዛግብት ይገልጻሉ፡፡ ይህም ወደ  ግእዝና አማርኛ ቋንቋ ሲመለስ ፍሥሕ (ደስታ)፣ ዕድወት፣ ማዕዶት (መሻገር፣ መሸጋገር)፣ በዓለ ናእት (የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት) ማለት ነው፡፡ የዚህም ታሪካዊ መነሻው በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ ሲኾን፣ ይህም እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት፤ ከከባድ ኀዘን ወደ ፍጹም ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህ ኦሪታዊ (ምሳሌ) በዓል አሁን አማናዊው በዓል በዓለ ትንሣኤ ተተክቶበታል ይላሉ የእምነቱ ተከታዮች፡፡

«ትንሣኤ» የሚለው ቃል ደግሞ የግእዝ ቃል መገኛው ‹ተንሥአ ተነሣ› የሚለው ግስ ሲኾን፣ ትርጕሙም መነሣት፣ አነሣሥ፣ አዲስ ሕይወትን ማግኘት ማለት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ይገልጻሉ።

ወዲህም የትንሳኤን ትርጉም በአምስት እንደሚከፈል የሃይማኖት አባቶች ይገልጻሉ። የመጀመርያው ትንሣኤ ሕሊና ነው፤ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ነው፡፡ ሁለተኛውም ትንሣኤ ልቡና ነው፤ የዚህም ምሥጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡ ሦስተኛው ትንሣኤ ለጊዜው (በተአምራት) የሙታን በሥጋ መነሣት ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሜ ሌላ ሞት ይከተለዋል፡፡ አራተኛው ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ያመላክታል፡፡

መዛግብት የበዓሉን አከባበር እንዲሚያስረዱት፤ በቅብብሎሽ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ፪ ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» ስትል የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡

ምንባቡ፣ ጸሎቱና ሌላውም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ ዲያቆኑ ነጭ ልብስ ተክህኖ ለብሶ፣ አክሊል ደፍቶ፣ መስቀል ይዞ፣ በጌታችን መቃብር በራስጌና በግርጌ በታዩት መላእክት ምሳሌ እንደ እርሱው ነጭ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ፣ ድባብ ጃንጥላ በያዙ፣ መብራት በሚያበሩ ሁለት ዲያቆናት ታጅቦ በቅድስት ቆሞ፡-«ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፣ ወከመ ኀያል ወኅዳገ ወይን፣ ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ፤ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደ ተወው ኃያል ሰውም ጠላቱን በኋላው ገደለ፤» የሚለውን የዳዊት መዝሙር በረጅም ያሬዳዊ ዜማ ይሰብካል፡፡

ካህናቱም ከበሮ እየመቱና በእርጋታ እያጨበጨቡ ተቀብለው ይዘምራሉ፡፡ ሕዝቡም በጭብጨባና በዕልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይኾናል፡፡ ይህ ምስባክ በዲያቆኑና በመላው ካህናት ሁለት ሁለት ጊዜ፤ በዲያቆኑና በመላው ካህናት አንድ ጊዜ (በጋራ) ይዘመራል፡፡ ይህም በድምሩ አምስት መኾኑ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ መሆኑ ይገለጻል።

መንፈቀ ሌሊት ሲኾንም ቅዳሴ ተቀድሶ ሥርዓተ ቍርባን ይፈጸማል፡፡ ከዚያም ሠርሖተ ሕዝብ ወይንም የሕዝብ ስንብት ከኾነ በኋላ ካህናቱም ሕዝቡ ወደየቤታቸው ሔደው እንደየባህላቸው ይፈስካሉ (ይገድፋሉ)፡፡

የመግደፊያ ዝግጅት ለሌላቸው ነዳያንም በየመንደሩ እየተዞረ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ» እየተባለ ከሥጋውም፣ ከአይቡም፣ ከቅቤውም ከመጣጣሙም፣ ከእርጐውም ይታደላል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ» እየተባባለ ይሰነበታል።

የዝንድሮ የፋሲካ ገበያ እንዴት ዋለ?

አዲስ ማለዳ ባለፉት ተከታታይ አመታት የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ የተለያዩ አካባቢዎች የምታደርግ ሲሆን በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት ጋር ገቢውን ማሳደግ ያልቻለው የማኅበረሰብ ክፍል፤ ወትሮውንም በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ቢሆንም፣ በበዓላት ወቅት ደግሞ በዓልን በወጉ ለማክበር ጫና ውስጥ ይገባል፤ በዘንድሮም ባለው የዋጋ ንረት ገበያው እንዴት ዋለ ስትል ቅኝት አድርጋለች።

የዘንድሮ የሽንኩርት ገበያ በዚሁ ዓመት መጀመሪያ ከነበረበት የተጋነነ ዋጋ በአንጻሩ የተሻለ ሆኖ በሰንበት ገበያዎች ከ40 እስከ 50 ብር በኪሎ እንዲሁም በመደበኛ ገበያዎች ከ60 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል።

እንዲሁም ዶሮ ከዝቅተኛው 800 ብር እስከ ከፍተኛው 1 ሺህ 500 ብር በተለያዩ የገበያ ስፍራዎች እየተሸጠ መሆኑ አዲስ ማለዳ የተመለከተች ሲሆን፤ አንድ ኪሎ ቂቤ በሳል እና ለጋ ከ800 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ነው።

በተመሳሳይም  የበግ ዋጋ ዝቅተኛው 5 ሺህ ብር፣ መካከለኛው 8 ሺህ 500 ብር እና ከፍተኛው ከ11 ሺህ ብር እስከ 20 ሺህ ብር በሆነ ዋጋ ግብይት እየተከናወነ ይገኛል።

በመንፈሳዊ በዓላት፣ አልፎ አልፎ ባዘቦቱ ወይም በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ማኅበረሰቡ በኅብረት ከብት እየገዛ በማረድ ቅርጫ ሲካፈል መመልከት ዘመናትን ያስቆጠረ የአብሮነትና የበዓል መገለጫ ነው በዝንድሮው ፋሲካ የበሬ በስንት ብር እየተገበያየ ነው ስትል አዲስ ማለዳ የጠየቀችሲሆን፤ ዋጋው በተለያዩ ስፍራዎች እንዲሁም በሬዎቹ አቋም የተለያየ ቢሆንም አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረግችበት ገበያ ዝቅተኛው 50 ሺህ ብር፣ መካከለኛ ከ70 ሺህ ብር ጀምሮ እንዲሁም ከፍተኛው 110 ሺህ ብር ድረስ የሚሸጥ መሆኑ ተረድታለች።

በተጨማሪም አንዳንድ አካባቢዎች አንድ በሬ ከ200 ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply