ፍርድ ቤቱ የኢቢሲ’ን ክርክር ውድቅ በማድረግ ወገን አበበ ወደስራው ለመመለስ ይግባኝ እንዲጠይቅ ፈቀደ 

ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሰራተኞችን በማጋለጡ ከሥራ የተሰናበተው ወገን አበበ፤ በተቋሙ የዲሲፕሊን ቅጣት ላይ ይግባኝ እንዲጠይቅ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ወሰነ። 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይግባኝ ሊፈቀድ አይገባም በሚል ላደረገው ክርክር፤ ከተቋሙ ያለአግባብ ከሥራዬ ተሰናብቻለው ያለው ወገን አበበ “የተሰናበትኩበት ደብዳቤ የተሰጠኝ ከተጻፈ 30 ቀናት በኋላ ነው። ይኼውም ይግባኝ ለመጠየቅ እንዳልችል ታስቦ ነው” በሚል በቅጣቱ ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚያስችለውን ውሳኔ ለማግኘት በኮሚሽኑ የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ሲከራከር ቆይቷል። 

የመንግስት ሠራተኞች በተቋማት በሚተላለፍባቸው የዲሲፕሊን ቅጣት ቅሬታ ካላቸው በዲሲፕሊን አፈጻጸምና የቅሬታ አቀራረብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 77/94 አንቀጽ 37(2) ድንጋጌ መሰረት ውሳኔው ለመንግስት ሰራተኛው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ለመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል ተደንግጓል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገለው ወገን አበበ በኢቢሲ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ “400 የሚሆኑ ሠራተኞች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ” እንዳላቸው አጋልጠሃል በሚል ከስራ መባረሩን ለአዲስ ማለዳ መናገሩ አይዘነጋም። 

ኢቢሲ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው የጽሑፍ አስተያየት “አመልካች [ወገን አበበ] በተቋሙ የተወሰነውን ውሳኔ እንዲያውቁትና እንዲወስዱት በግል ስልካቸው በተደጋጋሚ የተነገራቸው ሲሆን ለመውሰድ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል” ሲል ገልጿል። አክሎም “በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንዲለጠፍ ተደርጓል” በማለት ወገን አበበ የይግባኝ ጊዜ ያለፈው በቸልተኝነትና ውሳኔ እንደተሰጠ እያወቁ ለመውሰድ ባለመፈለጋቸው ነው በማለት ይግባኝ እንዳይፈቀድ መጠየቁን አዲስ ማለዳ ከጽሁፍ አስተያየቱ ተመልክታለች።

በዚህም ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ “ይግባኝ ባይ (ወገን አበበ) ያቀረቡት የይግባኝ ማስፈቀጃ ከአቅም በላይ የሆነ እና ተቀባይነት ያለው ምክንያት ሆኖ አግኝቶታል” ብሏል። በፍርድ ቤቱ እይታ በቸልተኝነት አለመሆኑን ይግባኙን ለአስተዳደሩ ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡ ያደረጋቸው በቂ ምክንያት በመኖሩ እንዲሁም የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ያላለፈ ስለሆነ  የአመልካችን አቤቱታ ተቀብሎታል በማለት ፍርድ ቤቱ ለወገን አበበ በመወሰን ይግባኝ እንዲከፈት ውሳኔ ሰጥቷል።

ውሳኔውን ተከትሎ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው ወገን ኢቢሲ ተጠሪነቱ ለፓርላማ ሆኖ እያለ “ይኼ ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለምን ዝምታን እንደመረጡ አልገባኝም፤ ይኼ ዝምታ ነው በተቋሙ ውስጥ ላሉ ሰራተኞች የልብ ልብ የሰጣቸው” ሲል ተደምጧል። በተጨማሪም በዚሁ ጉዳይ ላይ የፌደራል ጸረ ሙስና ኮሚሽን የስም ዝርዝር እያለው ምንም አይነት ጥያቄ አለማንሳቱ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጿል።

በተመሳሳይም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የወገን አበባ ጠበቃ ሰለሞን አበበ “ውሳኔው ለመስጠት የወሰደው ጊዜ በመደበኛ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ሲታይ አጭር ባይባልም አመልካቹ ስራ ላይ ካለመሆኑ ጋር ሲደመር ረጅም ነበር” ብለዋል። በዚህም ከመጋቢት 2 ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ይግባኛችንን አቤቱታ እንድናቀርብ፤ እንዲሁም ኢቢሲ ደግሞ ቅሬታ ካለው ይግባኙን ሕጉ በሚፈቅደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማቅረብ የሚችል መሆኑም አንስተዋል።

“ይሄ ሁሉ ወጣት ተምሮ ስራ ባጣበት አገር በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እስከ 57 ሺህ ብር ደሞዝ የሚበሉ ሠራተኞች አሉ። ይኼን ጉዳይ ማጣራት የሚፈልግ አካል ካለ ይጠይቀኝ፤ ስም ዝርዝሩን መስጠት እችላለው” የሚለው የኢቢሲ በማለት የማጣራት ሂደቱን መጀመር እንደሚቻል አንስቷል።

“እኔ ይግባኙን ማሸነፌ አለማሸነፌ አደደለም ቁም ነገሩ፤ ተቋሙ የእርምት እርምጃ መውሰድ አለበት። እስከ አሁን በዚሁ ጉዳይ ላይ እርምጃ የተወሰደበት ሰራተኛ የለም። አመራሮቹ ላይ እርምጃ ካልተወሰደ ሌሎች ሰራተኞችን ምንም ማድረግ አይቻልም። ይኼን ጉዳይ ሌላ አካል ገብቶ ነው ሊያስተካክለው የሚችለው” ሲል ወገን አበባ አሳስቧል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “በተሻለ ተቋሙን ለመቀየር እና አገሪቱን የሚመጥን ብሔራዊ ሚዲያ ለማድረግ የሪፎርም ስራ” እየሰራሁ ነው ሲል በሪፎርሙ በዋናነት የሠው ኃይል አቅም ማሳደግ፣ የሥራ ባህልን ማሻሻል እና በአገር ደረጃ የተጀመረውን የሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑን ከአንድ ዓመት በፊት አስታውቆ ነበር። 

ይሁን እንጂ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ በትምህርት ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን ሃሰተኛ መሆኑ በመረጋገጡ፤ በተቋሙ ውስጥ የቀረበው የሐሰተኛ እና እውቅና ያልተሰጠው የትምህርት ማስረጃ ጉዳይ በተቋሙ አመራር ደረጃ ያሉ እና ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን የሚነካ በመሆኑ “ለመሸፋፈን ጥረት መደረግ መጀምሩን” ወገን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጾ ነበር።

በዚህም ምክንያት ወገን ይኽ ጉዳይ ወደ ውጪ እንዳይወጣ በውስጥ በኩል ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱን የገለጸ ሲሆን “የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችም ሆነ የሠው ኃብት አስተዳደሩ፤ ይኼን ጉዳይ ከመፍታት ይልቅ ጉዳዩን ለመሸፈን እኛ ላይ ጫና ማሳደር” እንደጀመሩ ያስታውሳል። የእሱ ከሥራ መባረረም የዚህ አካል ነበር።

ኢቢሲ መስከረም 8 ቀን 2016 ለፌደራል የመጀምሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጻፈው ደብዳቤ ተቋሙ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ የተቋሙን ተዓማኒነት በከፍተኛ ደረጃ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተታቸው 10 ሚሊየን ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፈለኝ በማለት ጠይቆ ነበር። 

ሆኖም ግን ይኽ ክስ ለወገን አበበ እንዳልደረሰው የገለጸ ሲሆን፤ በአንጻሩ “ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት” ተከሶ ለፍርድ ቤቱ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በማቅረብ በነጻ መለቀቁ ይታወሳል። በመጨረሻም የኢፌደሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት በቅርቡ ያለአግባብ ከሥራ በመባበሩ ወደ ስራው እንዲመለስ ይግባኝ ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡ ጠበቃው ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply