You are currently viewing “…ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት ብቻ እንዲከበርለት ያድርጉልኝ ብዪ የምማጸንዎ እንደ መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ አባትና ወላጅነትዎም ጭምር ነውና ህጋዊ መብቱን አስመልሰው ልጄን ለቤቱ አ…

“…ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት ብቻ እንዲከበርለት ያድርጉልኝ ብዪ የምማጸንዎ እንደ መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ አባትና ወላጅነትዎም ጭምር ነውና ህጋዊ መብቱን አስመልሰው ልጄን ለቤቱ አ…

“…ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት ብቻ እንዲከበርለት ያድርጉልኝ ብዪ የምማጸንዎ እንደ መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ አባትና ወላጅነትዎም ጭምር ነውና ህጋዊ መብቱን አስመልሰው ልጄን ለቤቱ አብቅተው እናቱንም ከሞት ይጠብቁልኝ ስል እማጸንዎታለሁ፡፡” የጋዜጠኛ ክብሮም አባት የአርበኛውና ጡረተኛው ወርቁ አብርሃ የተማጽኖ ደብዳቤ! አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ታህሳስ 13 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠ.ሚ.ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለተከበሩ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አዲስ አበባ ይህን ግልጽ ደብዳቤ የምጽፍልዎ ዜጋ ፤ ለሀገሬ በብዙ ዓይነት መንገድ አገልግዬ በጡረታ ላይ የምገኝ ተራ ሰው ነኝ፡፡ ወደ እርስዎ የሚወስደኝ መንገድ ቢጠፋኝ፤ እነሆ በአየር ላኩልዎ፡፡ ጊዜዎ ፋታ ማይሰጡና በጣም ውስብስብ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዩች የተጣበበ መሆኑን ባውቅም፤ በሚያሸልቡበት ጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን በምናብዎ ደብዳቤዬን ያዩልኛል ብዬ በማሰብ ነው፡፡ ልጄ ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ፤ የአሀዱ ሬዲዩ የዜና ክፍል ሀላፊ እና አርታኢ ሲሆን፤ ከወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ አውሎታል፡፡ የእስሩ መነሻም የሆነው በዚህ ሬዲዮ ጣቢያ በተሰራ ዘገባ ምክንያት ሲሆን ፖሊስም “እጠረጥራቸዋለሁ”ብሎ ዜናውን የሰራችውን ጋዜጠኛና አለቃዋን ልጄን በተለያዩ ጊዜያት በቁጥጥር ሥር አውለዋቸዋል፡፡ በዚህ ቅሬታ የለኝም፡፡ በወንጀል የተጠረጠረ ሁሉ ህግ በሚፈቅደው መሠረት በቁጥጥር ስር ውሎ ወንጀሉ ቢጣራና እንደምርመራ ውጤቱ ወደ ፍ/ቤት ቢቀርብ ወይም ቢለቀቅ ተገቢ አሰራር ነው፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው ፍ/ቤት ከቀረበና በዋስ እንዲወጣ ከተወሰነለት በኋላ ፖሊስ ለመልቀቅ እምቢተኛ መሆኑ የእኔንም የህመምተኛ እናቱንም፤የአድናቂና የፍትህ ስርአቱን በእምነት የሚጠባበቁትን ሁሉ ቅስም ሰብሮአል፡፡ ለቀናት ደጅ ብንጠናም ከባድ የልብ ቀዶ ጥገና ያደረገውን ልጄን እንኳን የሚፈታልኝ ፤ያለበትን አውቃለሁ የሚለኝ አጥቼ ተጉላላሁ፡፡በመጦሪያዪ የታሰረ ልጄን ፍለጋ መንከራተት ብቻ ተረፈኝ፡፡ ፈጣሪ ያሳይዎ ይሄ ሁሉ እንግልትኮ ሬዲዮ ጣብያው ይቅርታ በጠየቀበት ሁኔታ ነው፡፡ ክቡርነትዎ ይህንን ጉዳይ ባለብዎት ሀላፊነት ላይ መጨመሬ ቢገባኝም ፤የአባትነት ግዴታየ የልጄ ንጽህና ረፍት ቢነሳኝ ፤የፍርድ ቤት ውሳኔ ተጥሶ ግልጽ ባልሆን አሰራር የት እንዳለ እንኳን በማላውቅበት ሁኔታየታሰረብኝን ልጄን ከእስር ለማስለቀቅ፤ ለኢትዮጰያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ለኢትዮጰያ እምባ ጠባቂ ተቋም፣ ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አመልክቼ አባከና የሚለኝ ባጣ እንጂ ሀገራዊ ሸክምዎን ረስቼ ላደክምዎ አይደለም፡፡ በርግጥ አንድ ነገር ይሰማኛል፡፡ ብዙዎች ንጹሀን ዜጎችና ጀግና አርበኞቻችን በገፍ ህይወታቸውን ለሀገራቸው ቤዛ እየገበሩ ባሉበት በዚህ ክፉ ቀን “አንድ ሰው ታሰረ ብሎ ማለት ምን ይባላል?” ተብዬ እንዳልወቀስ እሰጋለሁ ። አዎ ⵑ ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሀገራችን ጦርነት ላይ ናት ብለን መሃል ሃገርም በበለጠ ጥራትና ይዘት፣ ልማቱንም አገልግሎቱንም እያቀላጠፍን አገራችን ጦርነቱን በአሸናፊነት አድንድትወጣ ማድረግ እንጂ፤ ይህንን ሰበብ አድርገን በህግ ስም ህግን እንድንጥስ የመንግሥት መመሪያ የለም፡፡ ክብሮም ከሽብርተኛ ቡድኑ ጋር ግንኙነት የለውም ብቻ ሳይሆን፤ የሚጠየፋቸውም ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ባያዳላ ኖሮ ክብሮምን በአሀዱ ሬዲዮ፤ያውም በሀላፊነት ማግኘት ባልተቻለም ነበር፡፡ እናም ያሳደግኩት ልጄን በቅጡ አውቀዋለሁና ምስክርነቴ ለሀቅ ነው፡፡ ይልቁን አንድ ነገር ሳልወድ በግድ ልቤን ይቆረቁረኛል ይኸውም የታሰረው በስሙ ይሆንን የሚል። “ክብሮሙ ለክርስቶስ” (የክርስቶስ ክብር) እንዲል መጽሓፉ፤ ቃሉ የግዕዝ ነው፡፡ ግዕዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስለሆነም ትግርኛ ተጋርቶታል፡፡ ግዕዝ ከትግርኛም ቀዳሚ ነው፡፡ ታድያ ልጄን “ክብሮም” ብዬ መሰየሜ ምንድን ነው ሃጥያቴ?እርሱስ ቢሆን እኔ ባወጣሁለት ሥም ለምን ዋጋ ይከፍላል? ሳሳድገውም ኢትዮጵያዊ አድርጌ እንጂ የብሄር ስነ ልቦናን አላብሼ አልነበረም፡፡ በዚህ ደግሞ እኮራለሁ፡፡ አሁንም የልጄ የግፍ እስረኛ ክብሮምን ማንነት ለማወቅ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች የሠራቸው ኢትዮጵያዊነትንና ባለ ሀገርነትን የሚሰብኩ በርካታ ሥራዎቹ ምስክሮች ናቸው፡ ልጄ ክብሮም የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ ለመሆኑ ፖሊስ ቅንጣት (ሽርፍራፊ)ማስረጃ እንኳ ማቅረብ አልቻለም፤አይችልምም፡፡ ለዚህም ነው የዋስትና መብቱ አንዲከበር የመጀመሪያ ደረጃም፤የከፍተኛ ፍ/ቤትም ውሳኔ የሰጡለት ፡፡ ከዚህ በላይ፤ ንፅህናውን ለማሳዬት ተቀድዶ የተጠገነውን ልቡን ዳግመኛ ቀድዶ እንዲያሳያቸው መቼም አይጠበቅምና ክቡርነትዎ በወላድ አንጀት ራርተው መላ ያብጁለት ፤በአባትነት ስሜት ያለሁበትን ይረዱልኝ፡፡ እናቱንም ከሰርክ ለቅሶና ሀዘን ይታደጉልኝ፡፡ ከአያቱ ጀምሮ የኢትዮጵያ አርበኛ የአርበኛ ልጅ ነው፡፡ አያቱ በጣሊያን ወረራ በአርበኝነትና ከድል በኋላም በጦር ሰራዊነት ሀገሩን ከልቡ ያገለገለ ነው፡፡ በሶማሊያ ወረራ ጊዜም በ70 ዓመት እድሜው በአባት ጦርነት ኦጋዴን ዘምቶ የተዋጋ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እኔ አባቱም በሶማልያ ጦርነት፣ በኢትዮ-ኤርትራ በባድመ ግንባር የዘመትኩና ሚዛን የሚደፋ አኩሪ ተግባር የፈጸምኩ ነኝ፡፡ ፤ በኦጋዴን ግንባር ላይ ከእኛ አንድ ቤተሰብ ሶስት ሰዎች በግዳጅ ላይ ተገናኝተናል፡፡ አባቴ፣ እኔና ታናሽ ወንድሜ፡፡ ሁላችንም እዚያ የተገኘነው የወቅቱን የእናት ሀገር ጥሪ ተቀብለን ያለ ደመወዝ የዘመትን ነን፡፡ ታናሽ ወንድሜ እዚያው ሲሰዋ እኔና አባቴ መመለስ ችለናል፡፡ ይህን ሁሉ ያደረግነው ለአንዲት አገራችን ኢትዮጵያ ነው፡፡ እኔ በኦጋዴን ጦር ግንባር በቆየሁባቸው 3 ዓመታት ሙሉ ባስመዘገብኩት አመርቂ ስራ ከወቅቱ የሀገሪቱ የመከላከያ ሚንስትር ሌ/ጀ/ተስፋየ ገብረ ኪዳን በተፈረመ ሰርትፊኬት የታጀበ የአብዮታዊ ዘማች ሜዳልያ ተሸላሚ ነኝ፤ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ለ27 አመታት በግፍ ከገዛው ከቀድሞው ስርአት ጋር ጋር ባለኝ የተራራቀ የሃሳብ ልዩነት ምክንያት እና በማደርገው ትግል ሳቢያ ጭምር በ47 ዓመቴ ከመንግስት ሥራ በግፍ በመባረር ዋጋ የከፈልኩ ሰው ነኝ፡፡ እና ክብሮም ከዚህ ቤተሰብ ተወልዶ፣ በኢትዮጵያዊነት ሥነ ሥርዓት አድጎ፣እናት አገሩን የሚያደማ ባህሪይ ሊኖረው ከቶ አይችልም፡፡ ያልተዘራኮ አይበቅልም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፡፡ ችግራችን የልጄ መታሰርና መሰቃየት ብቻ አይደለም፡፡ በተመሰረተው ክስና ውንጀላ ልጄ በብዙ ሺዎች በሚቆጠሩ አድናቂዎቹ ዘንድ የነበረው መልካም ሥም እና ዝና ጎድፏል፡፡ ከርሱም አልፎ፤ በጽኑ ኢትዮጵያዊነት አቋማችን የምንታወቀው የኛ ቤተሰቦቹ ስምም አብሮ ጎድፏል ፡፡ የደረሰብን ሞራላዊ ውድቀት በምንም ካሳ ሊተካ የሚችል አይደለም፡፡ ነገር ግን ከእርሱ በህይወት መገኘትና ከቤተሰቡ መቀላቀል የሚብስ አይደለምና ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት ብቻ እንዲከበርለት ያድርጉልኝ ብዪ የምማጸንዎ እንደ መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ አባትና ወላጅነትዎም ጭምር ነውና ህጋዊ መብቱን አስመልሰው ልጄን ለቤቱ አብቅተው እናቱንም ከሞት ይጠብቁልኝ ስል እማጸንዎታለሁ፡፡ ድል ኢትዮጵያⵑ ውድቀት ለጠላቶቿⵑ አርበኛውና ጡረተኛው አባቱ ወርቁ አብርሃ፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply