ፍቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ተባለ፡፡በኢትዮጵያ የመኖርያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ሆነው ኢትዮ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ዘርፉ ላይ ህገወጦች እየተሳተፉበት በመሆኑ ስጋት ላይ ወድቀናል ብሏል፡፡

ሶስት ማህበራት የሚገኙበት ይህ ጥምረት ማለትም አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ገዳ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር እና ኢትዮ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ያካተተ ነው፡፡

ማህበራቱ ላለፉት 40 አመታት የኢትዮጵያ መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በህጋዊ መንገድ እየተጠቀሙ ባለበት ሁኔታ በህገወጥ የጥበቃ ስራ ላይ እየተሳተፉ ባሉ ዜጎች ምክንያት ስራቸው አደጋ እንደተጋረጠበት ነው የተገለጸው፡፡

ከማህበራቱ መካከል አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ዛሬ በሰጠው መግለጫ የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሃገር ውስጥ የስራ ስምሪት አገልግሎት ስለሚሰጡበት ሁኔታ ለመወሰን በወጣው መመርያ በኢትዮጵያ የመኖርያ ፍቃድ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው ሰዎች በዘርፉ እንዳይሳተፉ የደነገገ ቢሆንም ደንቡ ተጥሷል ብሏል፡፡

ማህበሩ አጣራሁት ባለው መረጃ መሰረት በርካታ ድርጅቶች ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው ጥበቃዎችን አሰማርተው በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ሲል አስታውቋል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ላሰማሯቸው ጥበቃዎች ደሞዝ ሲከፍሉ ጡረታ እንደማይቆርጡ ለመንግስት ግብር እንደማይከፍሉና የስራ ግብርም እንደማይከፍሉ ነው የተነገረው፡፡

ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቀውን ስራና ሙያ የሃገሪቱን ህግና ደንብ ወደ ጎን ብለው በገቡ ተቋማት ምክንያት ስራችንን አክብደውብናል በስራችን ላይ ጫናም አሳድረውብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን በሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 632/2001 እና አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ላይ እንደሰፈረው ማንያውም ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ወይም በኢትዮጵያ ቋሚ የመኖርያ ፍቃድ ለለው የውጭ ሃገር ዜጋ በምንም አይነት የጥበቃ ስራ ላይ አይሳተፍም የሚለው መመርያ ወደ ጎን በማለት ዘርፉ ላይ ተሰማሩ ዜጎች መኖራቸው ነው የተገለጸው፡፡

በመሆኑም መንግስት በነዚህ ድርጅቶች ላይ አስፈላገውን ማጣራት አድርጎ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ሲል ማህበሩ አስታውቋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

ሰኔ 07 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply