ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ ውሉን ለመፈራረም ፍቃደኛ ነኝ አለ።ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አ/ማ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር በውል እና ማስረጃ ለመፈራረም ፍቃደኛ ነኝ ብሏል።ፐርፐዝ ብላክ…

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ ውሉን ለመፈራረም ፍቃደኛ ነኝ አለ።

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አ/ማ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር በውል እና ማስረጃ ለመፈራረም ፍቃደኛ ነኝ ብሏል።

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አ/ማ በ1.5 ሚልዮን ብር ባለ 3 መኝታ አፓርትመንት እሰራለሁ ብሎበት የነበረው ሜክሲኮ የሚገኘው የመሬት ግብይት መቋረጡ ትናንት ተገልጿል።

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ እና በፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ትሬዲንግ አ/ማ መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር የሽያጭ ውል ለማሰር ባለመቻሉ ሂደቱ መቋረጡን ቢጂአይ-ኢትዮጵያ አሳውቋል።

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ የሽያጭ ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል እንዲኖር እና የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ሽያጩ እውን እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የገለፀ ሲሆን “በፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ትሬዲንግ አ/ማ በኩል ግብይቱን ለማጠናቀቅ እና የሽያጭ ውሉን ለመፈረም ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ምክንያት የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ሽያጭ ሂደቱን ለማቋረጥ ተገደናል” ሲል አሳውቋል።

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ እና የህግ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ኤርሚያስ ብርሃኑ በበኩላቸው ስምምነቱን በውልና ማስረጃ ለመፈራረም ፍቃደኛ ያልሆነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ነው ብለዋል።

በአንቀፅ 6 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት እንደዚህ አይነት ስምምነቶች በውልና ማስረጃ መፈራረም እንዳለበት የሚያስቀምጥ ቢሆንም ፍቃደኛ ያልነበረው ቢጂአይ ኢትዮጵያ እንጂ ፐርፐዝ ብላክ አይደለም ነው ያሉት።

የሽያጭ ውል ነበረን ያሉት አማካሪው ያለበትን ግዴታ ያልተወጣው እንዲሁም በውልና ማስረጃ ለመፈራረም ዝግጁ ባለመሆኑ እንዲዘገይ ሆኗል ብለዋል።

የተዋዋልነው ውል አንድ ወገን ተነስቶ ደስ ሲለው የሚያፈርሰው ተራ ውል አይደለም ያሉት ዶ/ር ኤርሚያስ ጉዳዩ በህግ የሚዳኝ ይሆናል ነው ያሉት።

በውል እና ማስረጃ በህጋዊ መንገድ እንፈራረም ብለን ቅዳሜ ዕለት ነው ደብዳቤ የላክነው ያሉት አማካሪው ፤ያለባቸውን የመንግስት ግዴታ መወጣት ባለመቻላቸው ይህን ደብዳቤ ሰኞ ዕለት እንደሚፅፉት እናውቅ ነበር ብለዋል።

ፐርፐዝ ብላክ ገዢ በመሆኑ ያለበት ግዴታ ገንዘብ መክፈል ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር ኤርሚያስ ፤ ሀላፊነቱን ያልተወጣው እና ጉዳዩ እንዲዘገይ ያደረገው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ነው ብለዋል።

ፐርፐዝ ብላክ የመጀመሪያ ዙር ክፍያ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ከፍሏል የተባለ ሲሆን፤ ውሉን ለመዋዋል እና ሁለተኛውን ዙር ክፍያ ለመክፈልም ፍቃደኛ ነን ነው ያሉት።

ከአንድ አመት በፊት የተዋዋልነውን ውል በውል እና ማስረጃ እናፅድቀው ያሉት ዶ/ር ኤርሚያስ ፤የሚጠበቅባቸውን የመንግስት ግብር ባለመክፈላቸው ግን እስካሁን ውሉን መፈራረም አልቻልንም ብለዋል።

ከአንድ ወገን በተነሳ ጉዳይ ሌላኛውን ወገን መተቸት አስፈላጊ አይደለም ያሉት የህግ አማካሪው ፤ ውሉን አፍርሰናል ሲሉ እንኳን እንደ ተዋዋይ ወገን በግልፅ አላሳወቁንም ነው ያሉት።

እኛ ቢፈልጉ ዛሬ ከሰዐት ቢፈልጉ ነገ በማንኛውም ሰዐት ለመፈራረም ዝግጁ ነን፤ ስለዚህ ቁርጠኝነት የሚለካው ውልና ማስረጃ በመዋዋል በህጋዊ መንገድ በማፅደቅ በመሆኑ እባካችሁ በውል እና ማስረጃ እናፅድቀው ብለን በተደጋጋሚ ስንጠይቅ ቆይተናል ብለዋል።

ይህ ውል ቢፈርስም ቤት ለመሸጥ ቃል ለገባንላቸው ደንበኞች ግን በተዋዋልነው 5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ቤቱን እናስረክባለን ብለዋል።

ከዚህ ቦታ በተጨማሪ ሌሎች ቦታዎች ላይ መሬት ገዝተን መሠረት እየጣልን እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል።

ከመንግስት በሊዝ ስምምነት እንዲሁም 30/70 በሚል ስምምነት በግዢ ሂደት ላይ ያሉ መሬቶች አሉ ብለዋል።

ቀደም ብሎ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በሜክሲኮ የሚገኘውንና የቢጂአይ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ዋና መሥሪያ ቤት አድርጎ ሲጠቀምበት የነበረውን ሥፍራ ለመግዛት መስማማታቸውን ከሁለቱም ወገን መገለጹ ይታወሳል።

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Source: Link to the Post

Leave a Reply