ፑቲን ከትራምፕ ይልቅ የባይደንን ፕሬዚዳንትነት እንደሚመርጡ ተናገሩ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይልቅ የባይደንን ፕሬዚዳንትነት እንደሚመርጡ ተናገሩ።

ባይደን የበለጠ ልምድ ያላቸው እና ሊገመት የሚችል ባህርይ ያላቸው ሰው ናቸው ሲሉም መናገራቸው በርካቶችን አስደንቋል።

ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ከመወዳደራቸው በፊት ፑቲን “ታላቅ እና ጎበዝ” ሲሉም በአውሮፓውያኑ 2016 አሞካሽተዋቸው ነበር።

ባይደን የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ፑቲንን ለዓመታት በሰላ ሁኔታ በመተቸት የሚታወቁ ሲሆን ከዩክሬን ወረራ በፊትም በአንድ ወቅት “ነፍሰ ገዳይ” ሲሉ ወርፈዋቸው ነበር።

ፑቲን በቅርቡ ከአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ታከር ካልርሰን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይም አስተያየት የሰጡ ሲሆን ጥያቄዎቹ የሰሉ እና የተስተካከሉ ስላልነበሩ እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት ከሩሲያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የባይደን አመራር ለሩሲያ የተሻለ እንደሚሆን የተናገሩት ፑቲን ምክንያቱንም ሲጠቅሱ “የበለጠ ልምድ ያለው፣ ሊገመት የሚችል ባሕርይ፣ ፖለቲከኛ እና መሰረት ያለው ሰው ነው” ብለዋል።

ፐቲን አገራቸው “የአሜሪካን ህዝብ አመኔታ ካገኘ” እና የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ካሸነፈ ከማንኛውም መሪ ጋር እንደምትሰራም በዚሁ ወቅት አብራርተዋል።

ባይደንን ከትራምፕ ይልቅ ቢመርጧቸውም የዩክሬንን ጦርነት ያወገዙበትን መንገድ “እጅግ ጎጂ” እና “ስህተት የተሞላው” ነው ሲሉ ፑቲን ገልጸውታል።

በአውሮፓውያኑ 2016 የአሜሪካ ምርጫ ወቅር ትራምፕ ከፑቲን ጋር “በጥሩ ሁኔታ እንደሚግባቡ ጠቁመው” ነበር።

የካቲት 07 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply