ፓርቲዎች በምዕራብ ጎጃም፣ ጅጋ ከተማ ‘ተፈጸመ’ ያሉትን ግድያ አወገዙ

አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በምዕራብ ጎጃም ጅጋ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ሃይሎች ተፈፀመ ያሉትን “የንፁሃን ግድያ” አወገዙ፡፡ እናት ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ባወጡት መግለጫ፤ የመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች፣ በምዕራብ ጎጃም ጅጋ ከተማ ውስጥ “የፈጸሙትን ጭፍጨፋ እንቃወማለን” ብለዋል።
ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ “የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በንጹሃን ላይ የፈፀሙት ግድያ፣ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ” ፓርቲዎቹ ከትላንት በስቲያ ሐሙሰ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
ፓርቲዎቹ፣ “የመንግስት ወታደሮች ጎህ በተባለ ሆቴል በመመገብ ላይ የነበሩ 12 ሰላማዊ ሰዎችን አሰልፈው ረሽነዋል” ሲሉ ከስሰዋል። የመንግስት ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ “የበቀል እርምጃ” የወሰዱት፣ ከጅጋ ከተማ ወጣ ብሎ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ እንደሆነ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
ከተገደሉት ሰዎች መካከል፤ የባንክ ሰራተኞች፣ መምህራንና የጉልበት ሰራተኞች እንደሚገኙበት ያመለከቱት ፓርቲዎቹ፣ “የመንግስት ሃይሎች ስድስት ሰዎችን ከንግድና መኖሪያ ቤቶች ጭምር እያስወጡ ረሽነዋል” ብለዋል። ሁለት በጥይት ተመተው የቆሰሉ ሰዎች በባሕርዳር ፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
“የፀጥታ ሃይሎች ጎዳና ላይ የምትኖር አንዲት የአዕምሮ ሕመምተኛን ጨምሮ ከሞባይል ቤት፣ ከፀጉር ቤትና ከመኖሪያ ቤት በማስወጣት ተጨማሪ 6 ሰዎች፣ በአጠቃላይ 18 ሰዎች መግደላቸውን  የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል” ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
“የመከላከያ ሰራዊቱ በንጹሐን ዜጎች ላይ የወሰደውን አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ እናወግዛለን” ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ የተፈጸመው ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራና በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። “ከታሪክ መማር ብልህነት ነው” ያሉት አራቱ ፓርቲዎች፤ በመንግስት በኩል ለድርድር ቦታ እንዲሰጥ አሳስበዋል። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፤ የመከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች ተፋላሚ ወገኖች ዓለም አቀፍ የጦር ሕግን እንዲያከብሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply