ፓትርያርኩ: የቅዱስ ሲኖዶሱን መግለጫ በንባብ ለማሰማት ፈቃደኛ አልኾኑም፤ መግለጫውን፥ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በንባብ አሰምተዋል

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G

የቅዱስ ሲኖዶሱን ጉባኤ በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ዛሬ ከቀትር በፊት የነበረውንም የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እየመሩ፣ የመግለጫው ረቂቅም ሲነበብ አስተያየት እየሰጡ ውለው ነው የወጡት፡፡ መግለጫውን ለመዘገብ ለ9፡00 የተጠሩት ጋዜጠኞች፣ ከሰዓቱ ቀደም እና በርከት ብለው በስፍራው ቢገኙም፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ እየተጠበቁ በመዘግየታቸው፣ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩን አግባብቶ ለማምጣት፣ ሦስት ብፁዓን አባቶች በምልአተ ጉባኤው ተመርጠው ቢላኩም፣ ቅዱስነታቸው፣ ከማረፊያቸው ወደ ቅዱስ ሲኖዶሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ መጥተው፣ መግለጫውን በንባብ ለማሰማት ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡ ለዚህም የተለያዩ አስተያየቶች በመንሥኤነት እየተጠቀሱ ይገኛል፡-

  1. “የምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባ ቀትር ላይ ሲጠናቀቅ፣ አንድ ብፁዕ አባት፣ መግለጫው፥ በዋና ጸሐፊው ይነበብ፤ የሚል አስተያየት ሰጥተው ስለነበር በዚያ ተከፍተው ይኾናል፤”
  2. “በጥብቅ የተቃወሙትና ፊርማቸውን ያላኖሩበት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ ማሻሻያ በመግለጫው በመካተቱ ተከፍተው ያን ላለማንበብ ይኾናል፤”
  3. አንድ መነኰስ ቀትር ላይ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በስልክ ጠርተውኝ ነው፤ እገባለኹ የለም አትገባም፤ በሚል ከቅዱስነታቸው የጥበቃ ሓላፊ ኢንስፔክተር ገብረ ጻድቃንና ሌላ ባልደረባው ረዳት ኢንስፔክተር መቻል ደሴ ጋራ በፈጠሩት አለመግባባት ተካሥሠው፣ ጠባቂዎቻቸው ቃል እንዲሰጡ ወደ ኹለተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸው አሳዝኗቸው ይኾናል፡፡”

ከብዙ ጥበቃ በኋላ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፣ ራብዓይ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በንባብ ተሰምቶ፣ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply