ፔሌ በ82 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

https://gdb.voanews.com/022a0000-0aff-0242-08ac-08dae9d63b55_w800_h450.jpg

በልዩ አስማታዊ የእግር ኳስ ችሎታው የሚታወቀው እና ባለፈው መዕተ ዓመት ከተፈጠሩት ስፖርተኞች መሪ ተደርጎ የሚታየው የብራዚሉ ዝነኛ የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ልጁ ዛሬ በኢንስታግራም ከለቀቀችው ዜና መረዳት ተችሏል። 

በባዶ እግር ከሚያስኬድ ድህነት፣ በዘመናዊ ታሪክ እጅግ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን የበቃው ፔሌ በትልቅ አንጀቱ ላይ እባጭ በመታየቱ ላለፉት ወራት ወደ ሆስፒታል ሲመላለስ ቆይቷል። 

በሙሉ ስሙ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ በመባል የሚታወቀው ፔሌ 1,281 ጎሎችን በማስቆጥር በዓለም ክብረ ወሰኑን አሁንም የያዘ ሲሆን፣ የዓለም ዋንጫን ሶስት ግዜ በማንሳትም ብቸኛው ተጫዋች ነው። 

በተለየ ብቃቱና፣ በተወዳጅ ፈገግታው የሚታወቀው ፔሌ እግር ኳስ በዓለም ተወዳጅ እንዲሆን አስተዋጽዎ አድርጓል ይባልለታል። ለሰባ ዓመታት በቆየ ስራውም በተጫዋችነትና ለስፖርቱ አምባሳደር በመሆን አገልግሏል። 

በእ.አ.አ ጥቅምት 23 1940 ዓ/ም በአንዲት ትንሽ የብራዚል ከተማ የተወለደው ፔሌ፣ እግር ኳስን ከአባቱ እንደተማረ ይነገራል። በከፊል ፕሮፌሽናል ተጫዋች የነበረው አባቱ በገጠመው የጉልበት ጉዳት ጨዋታውን አቁሟል። 

የልጅነት ግዜ ታሪኩም ሆነ ‘ፔሌ’ የሚለው ስም አመጣጥ አሁንም ምስጢር እንደሆነ ያመለክተው የሮይተርስ ዘገባ፣ በልጅነቱ ግብ ጠባቂ ሆኖ ሲጫወት የሠፈሩ ልጆች በአካባቢው በሚታወቅ አንድ ተጫዋች ስም ‘ቢሌ’ ብለው እንደጠሩትና በግዜ ሂደት ስሙ ወደ ‘ፔሌ’ እንደተቀየረ ፔሌ ከዚህ በፊት በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ተናግሮ ነበር። 

Source: Link to the Post

Leave a Reply