ፕሮስቴት ዕጢ ምንድነዉ?በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ በሽንት ፊኛ እና በታችኛዉ የሽንት ቱቦ መሀከል ያለ ዕጢ ነዉ፡፡ ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣ በመጠን እያደገ ይመጣል፡፡ በተለይ ደግሞ ዕድሜ ከ40…

ፕሮስቴት ዕጢ ምንድነዉ?

በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ በሽንት ፊኛ እና በታችኛዉ የሽንት ቱቦ መሀከል ያለ ዕጢ ነዉ፡፡

ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣ በመጠን እያደገ ይመጣል፡፡ በተለይ ደግሞ ዕድሜ ከ40 ዓመት በላይ ሲሆን ዕድገት ያሳያል፡፡

በሁለት ዓይነት መንገድም ያድጋል፡፡አንደኛዉ ወደ ዉጪ ሊያድግ ይችላል ሌላዉ ደግሞ ወደ ዉስጥ ወደ ሽንት ፊኛዉ ወይም የሽንት ቱቦ ዉስጥ ሊያድግ ይችላል፡፡

በዚህም የሽንት መተላለፊያዉን ስለሚዘጋ አንዳንድ ሰዎች ላይ ከሽንት ጋር በተያያዘ ችግሮችን ሊፈጥር ይችላል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የኩላሊት እና የሽንት ፊኛ ሀኪም ከሆኑት ከዶክተር ሙባረክ ባርጌቾ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

#የፕሮስቴት ዕጢ የሽንት ፊኛ ዉስጥ ማደግ ምን ችግር ሊያስትል ይችላል?

• ሽንት ሲሸኑ መቸገር ይኖራል

• ሽንት ለመሽናት ማስማጥ

• የሽንት መጠን እና አፈሳሰሱ ላይ ድክመት ሊኖር ይችላል

• ሽንት ለመጀመር መቸገር

• ሽንት ካለቀ በኋላ ተመልሶ የመሽናት ስሜት መሰማት

• ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ችግሩ ከፍ እያለ ሲመጣ ሽንት ለመቆጣጠር መቸገር

• በተደጋጋሚ ወደ ሽንት ቤት መሄድ ነገርግን ጠብ ጠብ የሚል ሽንት ብቻ መኖር

• ሌሊት ላይ በተደጋጋሚ ለሽንት መነሳት የሚታዩ ምልክቶች ናቸዉ፡፡

#እነዚህ ምልክቶችን ችላ ብንል ምን ይፈጠራል?

• የመጀመሪያዉ ተደጋጋሚ የሆነ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ነዉ፡፡

• በተለይ ዕድሜያቸዉ ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች ላይ በተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚፈጠረዉ በፕሮስቴት ዕጢ ምክንያት ነዉ፡፡

• ሽንት ስለማይወጣ እና የሽንት ፊኛ ላይ ሽንት ስለሚጠራቀም የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከፍ ብሎ እስከ ኩላሊት ኢንፌክሽን ሊደርስ ይችላል፡፡

• ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ሽንት በኩላሊቶች ላይ እንዲጠራቀም ስለሚሆን የኩላሊት መድከምን ሊያስከትል እና ከጥቅም ዉጪ ሊያደርግ ይችላል፡፡

• ስለዚህ እነዚህን ምልክቶች ስናይ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ያስፈልገናል ሲሉ ባለሙያዉ ይናገራሉ፡፡

#ህክምናዉ ታዲያ ምን ይመስላል?

• ሶስት ዓይነት የህክምና መንገዶች አሉ፡፡

• አንደኛዉ ምልክቶቹ አናሳ ከሆኑ እና ብዙም ችግር ያልፈጠሩ ከሆኑ በክትትል ማስተካከል ነዉ፡፡

• የሚወስዱትን የዉሃ መጠን በማስተካከል፣ የሚመገቧቸዉን ምግቦች በመምረጥ ማስተካከል እና ተጓዳኝ ህመሞች ካሉባቸዉ መቆጣጠር እንዲችሉ በማገዝ ማስተካከል ይቻላል፡፡

• ሁለተኛዉ ደግሞ መድሀኒት መስጠት እና በመድሃኒት ማስተካከል ይሆናል፡፡ መድሃኒቶቹ ግን የሚያድኑ ሳይሆኑ በሚጠቀሟቸዉ ጊዜ የሽንት ችግሮችን የሚያቃልሉ ናቸዉ፡፡

• ሶስተኛዉ የህክምና ዓይነት ደግሞ የቀዶ ህክምና ነዉ፡፡ የቀዶ ህክምና ግን ለሁሉም አይሰራም፡፡

• በዋነኝነት የሚሰራላቸዉ ሰዎች ሽንት መሽናት የማይችሉ ፣በሽንት ፊኛቸዉ ላይ ጠጠር የተፈጠረባቸዉ ፣ በፕሮስቴቱ ምክንያት ደም የቀላቀለ ሽንት የሚሸኑ እንዲሁም የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸዉ ሰዎች ቀዶ ህክምናዉ ያስፈልጋቸዋል፡፡

• አንዳንድ ጊዜ ግን ህሙማን እራሳቸዉ በሚያቀርቡት ሀሳብ የቀዶ ህክምናዉ ሊሰራላቸዉ እንደሚችል ዶ/ር ሙባረክ ይናገራሉ፡፡

በእስከዳር ግርማ
ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply