ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስከአሁን ከእስር ለምን እንዳልተፈታ እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ተሰጠ

ዕረቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብር ጉዳዮች ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ሀሰን አርጋው በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይ ላይ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲፈጽሙ፤ ወይም ያልፈፀሙበት ምክንያት ካለ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ሰኔ 27 ቀን 2014 ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

ሆኖም ትዕዛዙን እንዲፈጽም በፍርድ ቤት የታዘዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሃላፊዎች የሉም በማለት ጋዜጠኛ ተመስገንን በሕገወጥ መንገድ አስሮ እንደሚገኝ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ገልጿል።

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ፤ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመፈጸሙን አስመልክቶ፤ በትናንትናው ቀን ያቀረቡትን አቤቱታ ችሎቱ በዛሬው ዕለት ሰኔ 29 ቀን 2014 መርምሮ ትዕዛዝ ሰጥቶበታል።

አቤቱታውን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የፀረ ሽብር ጉዳዮች ችሎት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ሀሰን አርጋው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲፈጽሙ፤ ወይም ያልፈፀሙበት ምክንያት ካለ ቀርበው እንዲያስረዱ፤ ለነገ ሰኔ 30 ቀን 2014 ከሰዓት 8፡00 ሰዓት ቀጠሮ ተሰጥቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply