♦ በሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል በጊምቢና በአካባቢው በንጹሐን ዜጐች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ ! ሰ.አሜሪ…

♦ በሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል በጊምቢና በአካባቢው በንጹሐን ዜጐች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ ! ሰ.አሜሪካ:- ሰኔ 18/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል በጊምቢና በአካባቢዋ ይኖሩ የነበሩ ንጹሐን ዜጎች ወገኖቻችን አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም ይኖሩ በነበሩበት ቤታቸው በድንገት በደረሰባቸው አሰቃቂ ግድያና የነፍስ መጥፋት በመፈጸሙ ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ ሐዘን ተሰምቷታል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አገረ እግዚአብሔር እየተባለች ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባለ ቢጠራም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለው የርስ በርስ ግጭት በተለይም ሀገር ሰላም ብለው ከምንም ጉዳይ ጋር ንክኪ የሌላቸው ንጹሐን ዜጐች ላይ እየተፈጸመ ያለው ስደት፣ ግድያና ሞት ኢትዮጵያዊ መልካችንን የቀየረ እግዚአብሔርንም የሚያሳዝን ዕኩይ ተግባር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ታወግዛለች፡በተለይም በዕለቱ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያና ሞት በሕጻናት፣ በሴቶችና በሽማግሌዎች ላይ የተፈጸመ መሆኑን ሐዘኑን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ቀን ያልፍልናል ሕጻናት ልጆቻችንን አሳድገንና አስተምረን ለአገርና ለወገን መከታ ይሆናሉ በሚል ራእይ ማልደው እየተነሱ አምሽተው እየገቡ ነሯቸውን በረሀብ፣ በጥም፣ በራቁትነትና በሕመም እያሳለፉ የነበሩ ወገኖቻችን ይህም በዛባችሁ ተብለው በአሰቃቂ ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ግድያ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉ መላውን ዓለም አሳዝኗል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት አስከፊ ድርጊት ልማትን፣ እድገትና ብልጽግናን ለምትመኝ በዚህም ጎዳና ዳዴ እያለች ላለች ሀገር ቀርቶ ለሰለጠኑትና ላደጉትም አገራት የማይበጅ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻግሮ የመጣ ወራሪ ጠላት በሌለበት የግል ፍላጎትን ለማሟላት ሲባል በተደረገ የእርስ በርስ ግጭት መሆኑ እንደ አገር ሁላችንንም ሊያሳፍረን ሊደገምም የማይገባ ድርጊት ነው፡፡ ሰላም በዓለም ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱና ለአራዊቱ ለምድሩም ሆነ ለሰማዩ አስፈላጊ በመሆኑ ከእንዲህ ዓይነት የጥፋት ተልዕኮ መጠበቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ በዚህ ዓለም ሲኖር ሠራተኛው ሠርቶ ለመበልፀግ ነጋዴው ነግዶ ለማትረፍ በሽተኛው ድኖ በጤና ለመኖር ተማሪው ተምሮ ለማወቅ በአጠቃላይ ዜጐች ማልደው ለመውጣትም ሆነ አምሽተው ለመግባት በምድራችን ሰላም ሲገኝ እርስ በርስ መተማመን ሲኖር በመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ዜጐቻችን ለሰላምና ለአንድነት ተባብሮና ተከባብሮ ለመኖር እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንነሳበት ጊዜ አሁን መሆኑን ቤተ ክርስቲያናችን ታስገነዝባለች፡፡ ሀገራዊ ሰላም የሚገኘው በሰዎችና በሰዎች መካከል ኀብረት ሲኖር በመሆኑ መንግሥት በዜጐች መካከል ለጥላቻ ለአለመግባባትና ለመለያየት ምክንያት የሚሆነ በሰላምና በትዕግሥት በመቻቻልም ጭምር ለመኖር የማያስችሉ ድርጊቶችን ጊዜ ሳይሰጥ ከኅብረተሰቡ መካከል ነቅሶ ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ከዚሁ ጋር የዜጎች ሰላምና አንድነት የሚጠበቅበትን ሥራ ባለማቋረጥ ማከናወን የሚገባው መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡ በቀጣይም በየትኛውም የአገራችን ክፍሎች እንዲህ ዓይነት የጥፋት ድርጊት እንዳይደገም አስፈላጊው የዜጐች ጥበቃ እንዲደረግ አጥብቀን እናስገነዝባለን፡፡ እንዲሁም በግፍ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉትና በስደት ላይ አሁንም በሞትና በሕይወት መካከል እየተጨነቁ ለሚገኙ ወገኖቻችን አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እናሳስባለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ትመኛለች፡፡ በዚህ ዕኩይ ተግባር ሕይወታቸው ላለፉ ወገኖቻችንም እግዚአብሐር ነፍሶቻቸውን እንዲምርልን ትፀልያለች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላሙን ይስጥልን፡፡ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply