You are currently viewing ❝ነጻነት በነጻ አይገኝምና ኹሉም ለነጻነቱ ዋጋ መክፈልና የመታገል ግዴታ አለበት❞ ንግሥት ይርጋ  አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ     ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም         አዲስ አበባ ሸዋ…

❝ነጻነት በነጻ አይገኝምና ኹሉም ለነጻነቱ ዋጋ መክፈልና የመታገል ግዴታ አለበት❞ ንግሥት ይርጋ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ…

❝ነጻነት በነጻ አይገኝምና ኹሉም ለነጻነቱ ዋጋ መክፈልና የመታገል ግዴታ አለበት❞ ንግሥት ይርጋ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በአማራ ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ እንደ አርዓያ የምትወሰድ ታጋይ ናት። ትግሉን ቀደም ብላ የተቀላቀለች ቢሆንም የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል አከርካሪ የተሰበረበትን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከመሩት መካከልም ትጠቀሳለች። ድፍረት፣ ጽናት፣ ቆራጥነት፣ ደግነት እና አልደፈር ባይነት መገለጫዋ ነው። ሐምሌ 5/2008 የአማራ ሕዝብ ጠላቶች ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላትን ለማፈን ሙከራ ባደረጉ ጊዜ ወጣቶችን አስተባብራ በተኩስ ልውውጥ መካከል ወደ ኮሎኔል ደመቀ ቤት ያቀናች፣ በጥይት አረር ውስጥ ኾናም በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል እንዲቆም ድምጿን ከፍ አድርጋ ያሰማች ታጋይ ናት ንግሥት ይርጋ። በወቅቱም ሕዝባዊ አመጹን ተከትሎ በአሸባሪነት ተፈርጃ ለእስር ተዳርጋለች፤ መንግሥት አሸባሪ ብሎ የፈረጀው ትህነግ በቤተሰቦቿ ላይ ሳይቀር ከፍተኛ እንግልት እና በደል አድርሶባቸዋል፡፡ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ተጋግሎ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ከአራት ኪሎ ከወጣ በኋላ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ የትግል ስልቷን በመቀያየር የሕዝብን እና የሀገርን ሕልውና በማስቀጠል ሂደቱ ዐሻራዋን በጉልህ እያሳረፈች ትገኛለች። ንግሥት ጊዜዋን የምታሳልፈው ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ከፋኖና ሚሊሻ ጋር ግንባር በመሰለፍ ነው። በተጨማሪም ኀብረተሰቡን በማስተባበር ስለነጻነት ሕይወቱን እየገበረ ለሚገኘው የወገን ጦር ድጋፍ ታደርጋለች። ቀደም ብሎ የውኃ፣ የደረቅ ሬሽን እና የአልባሳት ድጋፍ ታደርግ ነበር ፤ አሁን ደግሞ በቋሚነት እንጀራ ማቅረብ ጀምራለች። ሰው በሞቀ ቤቱ በነጻነት ተቀምጦ የሚመገበውን የቁርስ፣ የምሳ እና የእራት አይነት ያማርጣል። የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ግን ብስኩት እና ቆሎ ተመግበው የሌሊት ቁር የቀን ሃሩር ተቋቁመው ነው የሚዋጉት። ሕዝባዊ ደጀንነት ለሠራዊቱ ትልቅ ጉልበት እንደኾነ የተገነዘበችው ንግሥት ደረቅ ሬሽን ብቻ ተመግቦ መዋጋት ከባድ እንደሆነ ገልጻለች። በዚህም ግንባር ከመሰለፍ ይልቅ በውጪ ሀገራት እና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበርና ገንዘብ በማሰባሰብ እንጀራ ማቅረብ ጀመረች። ❝ግንባር ላይ የሚዋደቁልን ጀግኖችን ውለታ አይደለም በእንጀራ በምንም ልንመልስ አንችልም❞ ያለችው ባለታሪካችን በማይጠብሪ ግንባር የጀመረችውን ውጤታማ ተግባር በጋሸና ግንባርም ጀምራለች። አሁን ለ28 ሠራተኞች ወርኃዊ ደመወዝ እየከፈለች እንጀራ በማስጋገር በሁለቱ ግንባሮች ለተሰለፈው የወገን ጦር በየዕለቱ ከ2 ሺህ እስከ 3 ሺህ እንጀራ በቋሚነት እያቀረበች ነው፡፡ በየቀኑ ለኹሉም የወገን ጦር እንዲዳረስ ማድረግ ባይቻልም ቢያንስ በሦስት ቀን ካልሆነም በሳምንት አንድ ጊዜ እንጀራ እንዲበሉ ማድረግ ለሠራዊቱ የሚሰጠው ደስታ ትልቅ ነው ትላለች። ለሥራው የሚሆን ተሸከርካሪ አለመኖር፣ የመንቀሳቀሻና የመሥሪያ ገንዘብ እጥረት እና የቁሳቁስ ችግር ስለነበር ስትጀምረው ከባድ ፈተና እንደነበረ ተናግራለች። ❝በሁሉም ግንባር ባደርገውና አቅርቦቴ በሠራዊቱ ልክ ቢደርስልኝ ደስታየ ነው❞ ያለችው ንግሥት የአቅም ውስንነት እንዳጋጠማት አስታውቃለች። በጋሸና ግንባር የአካባቢው መሥተዳድር ጤፍ፣ ዱቄት እንጨት እና የመሥሪያ ቦታ አመቻችቶላታል። ይህም ኾኖ ግን በበቂ ደረጃ ሠራዊቱን መመገብ እንዳልተቻለ ነው የጠቀሰችው። የገጠመን ችግር በሕይወት የመቀጠል እና ያለመቀጠል፣ እንደ ሀገር የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው። ሠራዊቱ በሚከፍለው መስዋእትነት ነው እኛ ሰላማችንን አግኝተን የምንኖረው። አሁን ግን በሠራዊቱ ተጋድሎ ብቻ ድል ማግኘት አስቸጋሪ ነው። “እንኳን ለነጻነት ለባርነትም መሥራት ያስፈልጋል፤ ለባርነት መሥራት ግዴታ ከሆነ ለነጻነት ዋጋ ብንከፍል ምን አለበት?” ስትል ትጠይቃለች። ነጻነት በነጻ አይገኝምና ኹሉም ለነጻነቱ ዋጋ መክፈልና የመታገል ግዴታ አለበት” ነው ያለችው። የእርሷን ተሞክሮ ዓይቶ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከወገን ሠራዊት ጎን በመቆም በመልካም ተግባር እንዲሳተፉም መልእክት አስተላልፋለች። በቁሳቁስ፣ በጉልበት ወይንም በገንዘብ ለማገዝ ፍላጎት ያለው ሀገር ነጻ እስከምትወጣ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቃለች። የሀገርና የሕዝብ ሕልውና ለማረጋገጥ የታጠቀና ያልታጠቀ ሠራዊት ወደ ግንባር እያቀና ነው። የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት ጦርነቱን በአሸናፊነት ለመደምደም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። እናም ሀገራዊ አንድነትን እና ሕዝባዊ ነጻነትን የሚሻ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያለችው። አሚኮ እንደዘገበው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply