‘ሀገርና ትውልድን ከታላቅ ውድቀት የመታደጊያ ማዕቀፍ’- ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

   ሀገራችን በኹለንተናዊ መንገድ እጅግ አስፈሪና አስጨናቂ ኹለንተናዊ ኹኔታዎች ውስጥ መኾኗ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ኹኔታ የዳረጉን በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት የምንላቸው እንጂ ኹሉን ጠቅልሎ የሚይዝ ነጥብ ማውጣት – አስቸጋሪ፣ ሰፊና ውስብስብ ከኾነው ባሕሪያዊና ጠባያዊ መገለጫው እንረዳለን፡፡ 

  ስለኾነም ከማዕቀፍ አንጻር ሰፊውን ባጭሩ፤ ውስብስቡን በነጠላ አቅጣጫ በማስመልከት ሀገርን ብሎም ትውልድን ከውድቀት የመታደጊያ ማዕቀፋዊ የመፍትሔ ሀሳቦችን እንመልከት፡፡ ይህም ማዕቀፋዊ ሀሳብ፡- 

 • አንደኛ፡– የሀገር ችግር በኹለንተናዊ መንገድ የተሳሰረ – ሰፊ፣ ጥልቅና ውስብስብ፣ ያለፉና ያሉ ሂደቶች ድምር ውጤት መኾኑን፤
 • ሁለተኛ፡- በኾነውና መኾን በሚገባው መሐከል ሰፊ ልዩነት ያለና የሚኖር መኾኑን፤
 • ሶስተኛ፡- ችግሮቹም በመጠን፣ በአይነት፣ በስፋት፣ በአድማስና በምንጭ የሚለያዩና ዛሬ የተፈጠሩ ሳይኾኑ ከትላንት ጀምሮ ሲንከባለሉ የቆዩና የሂደት ውጤቶችም እንደኾኑ፤
 • አራተኛ፡- ከአቅም አንጻር – በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚፈታ ኹለንተናዊ ችግር እንደሌለ፤
 • አምስተኛ፡- ትርጉም ያለው መፍትሔ የሚኖረው ከምንፈልገው ይልቅ ማድረግ በምንችለው ላይ ስንነሣ መኾኑን ከግንዛቤ በማስገባት ብሎም ያለንበትን ነባራዊ ኹኔታ/ዎች የሚፈቅዱትን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን በቅድሚያ ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

   ከላይ የተጠቀሱትን ዋነኛ ነጥቦች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሀገራችን መኾን ወደሚገባት ደረጃ በኹለንተናዊ መንገድ ለመድረስ ማድረግ ከሚቻለው ነባራዊ ጥሬ ሃቆች (Reality) መሠረት በማድረግ “ሀገርና ትውልድን ከውድቀት እንዴት እንታደግ?” ለሚለው ዐቢይ የወቅቱ ጥያቄ በመኾኑ የመፍትሔ ሀሳቦችን ከጊዜ ማዕቀፍ አንጻር እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

 1. በአጭር ጊዜ
 2. “የዜጎች ደህንነት ማስጠበቂያ አዋጅ” ማውጣት፤

   ከሀገራችን የረዥም ጊዜ ታሪክና የአኗኗር ዘይቤ ስንመለከት የሃይማኖት መቻቻልና አብሮ በሰላም የመኖር ዕሴት እንደነበረንና እንዳለን በአለም የታወቀ ነው፡፡ ስለኾነም ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የመንቀሳቀስና የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብት ያለው በመኾኑ ይህን የሚሸረሽሩ፣ አደጋ ላይ የሚጥሉና በተግባር የሚረግጡ አስተሳሰብና አመለካከቶች፣ እውቀቶችና ድርጊቶችን በየትኛውም ቦታና ጊዜ – በግለሰብ፣ በቡድንም ኾነ በተቋም ደረጃ በምልክት ደረጃ እንኳ ቢታይ ፈጣን እርምጃ (zero tolerance) ሊወሰድ የሚገባው ከመኾኑም በላይ ከጉዳዩ እጅግ አሳሳቢነት (serious) አንጻር ደግሞ ጉዳዩ በፌደራል በልዩ ኹኔታ የሚታይ – ቅጣቱም እጅግ ከፍተኛና ዋስትና የሚያስከለክል አዋጅን ማውጣት የግድ ይላል፡፡

 • የባሕል ክፍልን እስከታች መዋቅር በማውረድ፤

  በሀገራችን ከባቢዎች እርስ በራስ እንዲተዋወቁ – በየአካባቢው ያሉትም እንዲለሙና አንደኛው የሌላውን እንዲያውቅና በባለቤትነት ስሜት እንዲይዝ፤ የውይይት ባሕልን እንዲያዳብር፤ የሽምግልና ክብር እንዲጎላና ተገቢው ቦታ እንዲሰጠው፤ የትውልድ ቅብብሎሽ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ፤ ለባሕል ኢንዱስትሪ ልማት ዋነኛ የጀርባ አጥንት የሚኾን – – – በዋናነት ይህን ሥራው ያደረገ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር እንደአንድ ትልቅ ክፍል መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

 • ሕዝባዊ በርካታ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፤

   በሀገራችን በተፈጠሩ ኹለንተናዊ ቀውሶች ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደየግንዛቤያቸው፣ ዕድሜያቸው፣ ሞያቸውና እንደ-ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር እንዳላቸው ቅርበት ለያይቶ – ግልጽ፣ አሳታፊና ቅንነት የተሞላበት ሀገራዊ የውይይት መድረኮችን ያለ ፖለቲካዊ፣ ያለ ሃይማኖታዊ፣ ያለ ጾታዊ – – – ወዘተ ልዩነት ዜጎችን የሚያሳትፍ ሀገሪቱ ስላለፈችበት፣ ስላለችበትና ለወደፊት ሊያጋጥሟት ስለሚችሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ግንዛቤ የማስጨበጫ፣ ሀሳብ የመቀበያ፣ ፍላጎትን የማሳያ፣ ጥያቄ የመጠየቂያ፣ የመመለሻ፣ የማረሚያና የባለቤትነት ስሜትን የማዳበሪያ ሕዝባዊ መድረኮችን በብዛትና በጥራት ማዘጋጀት፤

 • የስብሰባ አጀንዳ፣ የዕቅድ አዘገጃጀትና የበጀት አጠቃቀምን ትርጉም ባለው መንገድ በመመልከት፤

  በሀገራችን እጅግ የዘቀጠና የወረደ የስብሰባ ብዛት፣ የዕቅድ አዘገጃጀትና የበጀት አጠቃቀም በተለያዩ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች የሚታይ የአደባባይ ምሥጢር በመኾኑ ስብሰባ ለምን? በምን? ስለምን? ከነማን? ጋር የዕቅድ ዝግጅት መቼ? በምን? ምን ለማሳካት? ለምን? ከምን በመነሣት? መለኪያውስ ምንድነው?

  የበጀት አጠቃቀም፡ በአለም በኢኮኖሚ መለኪያዎች እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ያለን ኾነንና ከፍተኛውን በጀታችንን በብድርና በእርዳታ የምንሸፍን የድሃ ድሃዎች ኾነን በሌላ በኩል ችግራችን ሰፊና ውስብስብ ኾኖ እንኳንስ በጀት የሚያስመልስ በጀት በእጅጉ የሚያስጨምርና የሚያስፈልገው እንደኾነ እየታወቀ የበጀት አጠቃቀማችን የተዝረከረከ፣ የፕሮጀክቶች አቀራረጽ – አዘገጃጀትና አፈጻጸማችን እጅጉን የተደነባበረና የወረደ፣ ትርጉም የሌላቸው የስብሰባና የፕሮፕጋንዳ ወጪዎቻችን እጅግ ከፍተኛ፤ ይባስ ብሎ በዝች የድሃ ድሃ ሀገር በጀት ሊዘጋ ሲል ላለመመለስ የሚደረገው የቀን ከለሊት ወጪ የማውጫ ሩጫና ይህ ኹሉ ተደርጎ አላልቅ ሲል መመለስ ሀገራዊ ውርደትና ትልቅ የአመራር ዝቅጠት በመኾኑ ለዚህ ትኩረት መስጠት አማራጭ የሌለው የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡

 • ሚድያን፣ ባለሙያዎችንና ከምሁራን ጋር የሚያገናኝ መስመር በሀገር ደረጃ በመዘርጋት – የተዘረጋውን በማጠናከር፤

   በሀገር ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚድያ አካላት፣ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችና በተለያየ መስክ የሠለጠኑ ምሁራን ስላሉበት ነባራዊ ኹኔታ፣ በሀገር ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ/ዎች ስላላቸው ሀሳብ፣ ስለሚፈልጉትና ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ከሚመለከተው አካል ጋር እንደዜጋነታቸው የሚገናኙበት መስመር መዘርጋትና የተዘረጋውንም መስመር የማጠናከሪያ መንገድ ላይ መመካከር፤

 • የመንግሥት አካላት አመራሮችን በማጥራት፤

  በመንግሥት አካላት (ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ ፈጻሚ) ውስጥ ያሉ አመራሮችን ከላይ እስከ ታች ለቦታው ምን ያስፈልጋል? ከሚል ግልጽ መነሻ ለቦታው ይመጥናሉ? እንዴት? በምን? ብሎ ከላይ እስከ ታች መገምገም፤ መገምገሚያው – ነጥብም በዋናነት ቦታው የሚፈልገውና ሀገሪቱ ያለችበት ኹኔታ/ዎች ሊኾኑ ይገባል፡፡

  በዚህም የማይመጥኑትን ወደ ሚመጥኑበት ቦታ ማሸጋገር – ፈጽሞ ብቁ ያልኾኑትን ያለ ምንም ርህራሄ ማሰናበት የግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ስለጥቂቶች ተብሎ ብዙዎች ትላንት የከፈሉት ኹለንተናዊ ዋጋ ሳያንስ ለዛሬና ነገ ትውልድ ላይ ዋጋ እንዲያስከፍሉና አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያሳርፉ እድል መስጠት ሀገርና ትውልድን መግደል ነው፡፡  

 • ሀገራችን ምን ላይ እንዳለች እውነተኛ (Real) ምስል በማስቀመጥ፤

   ሀገራችን ዕውን በኹለንተናዊ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መለኪያዎች ከአለም ሀገራት አንጻር ምን ላይ ነች? መኾኗስ ማረጋገጫው ምንድነው? ለዚህ የዳረጓት ዐበይት ዋና ዋና ምንጮችስ ምንድናቸው? እነዚህን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ኹኔታ/ዎችና ተግዳሮቶች ምንድናቸው? የሚለውን መፈተሽና ከእንቀስቃሴው ነጻ በኾኑ አካላት ማረጋገጥ፤

 1. በመካከለኛ ጊዜ
 2. የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ዕሴቶችን በማዳበር፤

  እንደሀገር ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ መዳበር ወሳኝ የኾኑ የምክንያታዊነት፣ የግልጽነት ባሕል፣ የተጠያቂነት አሰራር፣ የአሳታፊነት ሙሉ ልብና ቅንነት፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን የሚያዳብር ኹለንተናዊ ተግባራትን በኹለንተናዊ መንገድ ማከናወን፤

 • ከጠላትነት ትርክትና ከትላንት ማዕቀፍ ኹለንተናዊ ቅኝ ግዛት ነጻ በመውጣት፤

  በሀገራችን የሥልጣን ፖለቲካ ባሕል ውስጥ ያለውን ነገሮችን ከጠላትነት አንጻር የማየት፤ ጠላት የመፈለግ፣ ችግሮችን ከእውነተኛ መንሥኤዎቻቸው ውስጣዊ ይልቅ አስተዋጽዖ ወደ ሚያደርገው ውጫዊ የማድረግ፤ ራስን ከማጠናከር ባሻገር ሌላውን ከማዳከም ስልት፣ ጠላትነትን የሕልውና መሠረት ከሚያደርግ ትርክት በኹለንተናዊ መንገድ ነጻ ለመውጣት መንቀሳቀሰ፤

  ዕቅድና አፈጻጸምን ከትላንት አንጻር – ከሞተና ከወደቀ ሥርዓት ጋር ራስን ከማነጻጸር – ዕቅድን መድረስ ከሚገባንና ከምንችለው የነገ ማዕቀፍ ይልቅ ትላንት በተሰራ ሥራ ላይ መሠረት አድርጎ ዕቅድ የማውጣት የሀሳብ ድሃነት ተግባራት በኹለንተናዊ መንገድ በመግለጫዎች፣ በንግግሮችና በጽሑፎች ላይ ከአስተሳሰብና አመለካከት፣ ከእውቀትና ከተግባር አንጻር ነጻ የማድረጊያ እንቅስቃሴን ማዳበር፤

 1.  ከጥቃቅንና አነስተኛ ሀሳቦች ወደ ዕሳቤ፤ ከርዕዮተ ዓለም ወደ ርዕዮተ ሀገር የሚያሸጋግር ድልድይ በማበጀት፤

   ምላሹን ኹለንተናዊ የውስጥና የውጭ ኹኔታዎችን መርምሮ አዋጪ መንገድ ለማስቀመጥ ሰፊ ጊዜ የሚፈልግና እንደድልድይ ቢያንስ እንደሀገር ዕሳቤያችን ምንድነው? መነሻችንስ ከየት ነው? መድረሻችንስ ወዴት ይመስላል? የአለም ነባራዊ ኹኔታ ከኛ አንጻር በምን ኹኔታ ላይ ነው? በዚህ ሂደት እኛ ምን አይነት ሀገር እንሻለን? ለዛስ ምን ያስፈልጋል? ለምንፈልጋት ሀገር ምን አይነት ርዕዮተ ሀገር ያስፈልገናል? ተግዳሮቱ፣ ፈተናዎቹና ምቹ ኹኔታዎቹስ ምን ምን ናቸው? የሚሉ ትርጉም ያላቸው ከጥቃቅንና አነስተኛ ንትርኮችና ትኩረቶች እንደሀገር ወደ ዕሳቤያዊ፣ ሀሳባዊና ተጠይቃዊ የሚያሸጋግሩንን ጥያቄዎች ቢያንስ እንደጥያቄ ማንሣት ከማንኛውም ጊዜ በላይ በዚህ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

 1.  ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ፤ገዥነት ወደ መሪያዊነት ለመሸጋገር የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በማከናወን፤

   በኹለንተናዊ መንገድ ከነበርንበትና ካለንበት ነባራዊ ኹኔታ ወደ ምንፈልገው ለመሻገር ሂደትነቱ እንደተጠበቀ ኾኖ ሂደቱ የሚፈልገውን ቅድመ ኹኔታዎች የመለየት፣ የማደራጀትና የመቅረፍ ተግባራትን ማከናወን፤

 1.  የሚድያን እንቅስቃሴ ከእኛነታችን አንጻር በመመልከት፤

  በማንኛውም ኹኔታ/ዎች የሚድያዎች አስፈላጊነት ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ሚድያዎች ትላንትም፣ ዛሬም ኾነ ነገ ያስፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ከማስፈለግ በዘለለ ትርጉም ወዳለው ምልከታ ስናመጣው በየትኛውም የአመክንዮ መለኪያ ከወሰድነው ሚድያ መሣሪያ (Means) እንጂ ግብ (Goal) አልያም መጨረሻ (End) ሊኾን አይችልም፡፡ ስለኾነም ያሉን ሚድያዎች ከሚሰሩት ተግባር፣ መስራት ከሚገባቸውና እኛ ካለንበት አንጻር ትኩረት አድርጎ መመልከት፤

 1.  ከኃላ ቀርነት ለመላቀቅ በመትጋት፤

  ምንም እንኳ እንደሀገር ረዥም ታሪክ ካላቸው ሀገራት መሐከል የምንመደብ ቢኾንም ለፓርቲ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ባሕል፣ ለሀሳባዊ የውይይት ባሕል (ልዩና ተቃራኒ ሀሳቦችን የማስተናገድ)፣ የዲሞክራሲያዊ ዕሴት፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የአርቆ አሳቢነት፣ የዕምነት እድገት፣ የተቋማዊነት አስተሳሰብና አመለካከት – – – ባሕል ያላዳበርንና ኃላ ቀር በመኾናችን ከዚህ ሊያወጣን የሚያስችል ተግባራትን ማስቀመጥና በተግባር ማረጋገጥ፤

 1.  ሀገራዊ ቁጭትን በመፍጠር፤

   ሀገራችን የረዥም ጊዜ ታሪክ ካላቸው ቀዳሚ የአለም ሀገራት አንዷ ብትኾንም በብዙ መለኪያዎች ዝቅተኛ ደረጃ ያላትና ስሟ በአሉታዊ መገለጫዎች ተደጋግሞ የሚነሣ በመኾኑ ከመባላችን በላይ በመኾኑ የሚሰማው፣ የሚቆጭና የሚያነባ ትውልድን ለማበራከት ኹለንተናዊ ተግባራትን ማከናወን፤ 

 1. በረዥም ጊዜ
 2.  ሀገራዊ ማዕቀፍን (National Framework) በማበጀት፤

  እንደሀገር በኹለንተናዊ መንገድ ከነበርንበት፣ ካለንበትና ከምንፈልጋት ሀገር አንጻር በመካከለኛ ጊዜ ላይ የተነሡ ጥያቄዎችን መመለስ ምን አይነት ሀገር ነው የምንፈልገው? ኹለንተናዊ ልዩነቶችን መሸከም የሚችል ሀገራዊ ርዕያችን፣ ሀገራዊ ግባችን (የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ)፣ ሀገራዊ ዓላማችን (ዋናና ዝርዝር)፣ ሀገራዊ ተልዕኳችንስ – – – ምንድነው? ትርጉም ባለው መንገድ ሰፊ፣ ጥልቅ፣ ጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ ማስቀመጥ፤

 1.  የትምህርት ሥርዓታችንን በእኛነታችን ላይ የተመሠረተ እና ከአኗኗር ዘይቤያችን ጋር የተሳሰረ በማድረግ፤

  እንደሀገር እጅግ ባዕድ፣ በእኛነታችን ላይ ያልተመሰረተና ከአኗኗር ዘይቤያችን ጋር ያለው ትስስሮሽ የላላውን የትምህርት ሥርዓት ከላይ በተራ ቁጥር 15 በሚቀመጠው መልስ ላይ መሠረት የሚያደርግ በእኛነታችን ያለፈ፣ ያለና የምንፈልገውን ማንነት ብሎም ከምንኖረውና መኖር ከምንፈልገው የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተገናዘበ የትምህርት ሥርዓት ከላይ እስከ ታች መቅረጽና መዘርጋት፤

 1.  የሀገራዊ አምዶችን ትርጉም ባለው መንገድ በመጠቀም፤

  ለሀገር ግንባታ (Building Nation) እና ሕብረተሰብን ለማነጽ (Reshaping Society) በድምሩ ለሀገራዊ ማዕቀፍ (National Framework) የማይቋረጥ ሂደት ወሳኝ አምዶች የኾኑትን ትምህርት፣ ባሕልና ታሪክ ከኹሉ በላይ ተመጋጋቢ በኾነ መንገድ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ፤

 1.  ተቋማዊነትን ታሳቢ ያደረገ ሂደት በመከተል፤

   እንደሀገር የሕልውናችን ማስተማመኛ አኹን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን የተቋማዊነት ሂደት ነው፡፡ በግለሰቦችም ኾነ በቡድኖች ሕልውና ላይ ያልተመሠረተ ማንም መጣ – ማንም ሄደ የሚኖር፤ የተለያየ አስተሳሰብና አመለካከትን ማስተናገድና መሸከም የሚችል፤ ሀገራዊ ማዕቀፍን መነሻውና መዳረሻው ከኹሉ በላይ መሠረቱ የሚያደርግ ተቋማዊነትን በኹለንተናዊ መንገድ ትውልዶችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ በእምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት) ፣ በእውቀት (ዘመኑ በደረሰባቸው አሰራሮችና በሚጠቀምባቸው ስልቶችና ስትራቴጂዎች) እና በተግባር ደረጃ በኹለንተናዊ መንገድ መስራት፤

 1.  የኢትዮጵያውያን አሳቢ ተቋም በማቋቋም፤

   እንደሀገር አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ባለሙያዎችና ምሁራን ከፍ ባለ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ስለሀገራቸው ኹለንተናዊ ያለፈ፣ ያለና የሚመጣ ሂደት – ማሰብ፣ መመራመር፣ ነባር ዕሳቤዎችን የማዳበርና አዳዲስ ዕሳቤዎችን የማመንጨት – የማስፋት፣ ሀገራዊ የመንፈስ መግባባትን የሚያዳብሩ ተግባራትን የሚያከናውኑበት፤ የኢትዮጵያውያንን የርስ በርስ ዜጋዊ ኹለንተናዊ ሕብረትና አንድነት የሚያጠናክሩ ኹለንተናዊ ተግባራትን የሚሰሩበት ትልቅ ነጻ ተቋም ማቋቋም፤

 •  የባሕል ኢንዱስትሪ ልማትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ኹሉ ማዕከልና አካል በማድረግ፤

   ሥነ – ጽሑፋዊ ጥበቦች (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ የኾኑ ማንነቶቹ የሚገለጹባቸው ድርሰቶች (ልብ ወለዶችና ኢ ልቦለዶች)፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ ሥነ ቃሎች፣ መነባንቦች – – – ወዘተ)፤ እይታዊ ጥበቦች (የሥዕል፣ የፎቶ ግራፍ፣ የምልክት ሥራዎች፣ የፊልም፣ የድራማ፣ የጭውውት፣ የኪነ – ህንጻ ሥራዎች፣ የፋሽን፣ የዲዛይን፣ – – – ወዘተ)፤ ትዕይንታዊ ጥበቦች (የሙዚቃ፣ የትያትር፣  የውዝዋዜ፣ የጭፈራ፣ ባሕላዊ የሐዘንና የደስታ መገለጫዎች የኾኑ ተግባራት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ የሃይማኖት በዓላት መገለጫዎች)፤ የዕደ ጥበብ ሞያ (የእንጨትና የቆዳ ሥራ፣ የሽመና ሥራ ፣ የጌጣ ጌጥ ሥራ – – – ወዘተ) ሥራዎችን ከሀገራዊ ማዕቀፍ፣ ሀገራዊ ርዕይና ሀገራዊ አምዶች (ትምህርት፣ ባህልና ታሪክ) ጋር በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲስተሳሰርና እንዲዋሃድ መስራት፤  

    እነዚህ ከተደረጉና በአግባቡ በኹለንተናዊ አቅጣጫ ተገቢው ትኩረትና ምላሽ ካገኙ እርስ በራሳቸው እጅግ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸውና የማይነጣጠሉ በርካታ በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋማት ደረጃ የሚነሱ የፖለቲካ ምህዳርን ያሰፋል፤ ነጻነትን በተቋማዊነት ያስጠብቃል፤ ፍትሕን ለማስፈን ያስችላል፤ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ምቹ ኹኔታን ያበራክታል፤ መልካም አስተዳድርን በኹለንተናዊ መንገድ ያረጋግጣል፤ ሀገራዊ የመንፈስ መግባባትና የባለቤትነት ስሜትን ያሰርጻል፡፡ ያሳያል፡፡ ያዳብራል፡፡ ዜጎች እርስ በራሳቸው በእጅጉ የሚተማመኑ፣ የሚረዳዱ፣ የሚደጋገፉ፣ የሚጠያየቁ፣ የሚተሳሰቡና በማንነታቸው የሚኮሩ ይኾናሉ፡፡ በተግባርም ሀገራችን ወደ ላቀና ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሳትን መንገድ እንድትይዝ ያደርጋል፡፡

  ይህም ሲኾን በኹለንተናዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ከመለያየት ይልቅ የማቀራረብ ሥራ መስራት፤ ከሴራና ከማስመሰል መራቀ፤ ከማንም የግለሰብ፣ ቡድን ኾነ ተቋም አሽከርነትና ገረድነት ነጻ ወጥቶ – በዕሳቤና በሀገራዊ ርዕዮት ትውልዱን መምራት፤ በተራ ፍሬ ከርስኪ የአደባባይ ድራማዎች አለመታጠር፤ በጥቃቅንና አነስተኛ የኮስሞቲክስ ፖለቲካ አለመዋጥ፤ ከራሱ አልያም ከቡድናዊ ፍላጎት በላይ የሀገርና ሕዝብ ፍላጎትን ማሠልጠንን የግድ ይጠይቃል፡፡

   ከላይ የተጠቀሱ 20 ሀገራችንንና ትውልድን ከኹለንተናዊ ውድቀት የመታደጊያ ማዕቀፋዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎች በራሳቸው በጊዜ ሂደት የሚዳብሩ፣ አቅም ሲያድግ አብረው የሚያድጉ፣ እርስ በራሳቸው የማይቋረጥ ባሕሪያዊና ጠባያዊ ትስስር ያላቸውና ውጤታቸውም ኹለንተናዊ (Multidimenstional) መኾኑን በእጅጉ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

   በመኾኑም እንኳንስ በኹለንተናዊ መንገድ የሚፈልጓትን ሀገር ይቅርና በነጠላ በግለሰብ ደረጃ እንኳ የሚፈልጉትን አይነት ሰው ለመኾን ያለው ውጣ ውረድ እጅግ ከፍተኛ፣ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ትዕግስትን የሚጠይቅ፣ መውደቅ መነሣት ያለበት፣ እውቀትን፣ እምነትን፣ ጠንክሮ መስራትን፣ ተስፋንና አለማንቀላፋትን ግድ የሚል ነውና እንደሀገር ዜጎች የሚፈልጓትን ሀገር ለማየት ይህን ሂደት ማለፍ የግድ አማራጭ የሌለውና ሊኖረው የማይችል መኾኑንን መረዳት የግድ ይላል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply