“መረዳት እና ጊዜ” ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

   ሰው በተፈጥሮው ነገሮችን መረዳት የሚችልበት ተፈጥሯዊ ማንነት ብሎም በሂደት የሚዳብር ክህሎት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይህም ኹለንተናዊ ሂደት በጊዜ የተገደበ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ማንኛውም ዓይነት ኹለንተናዊ ልዩነት ቢኖረው እንኳ ይጸነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል ብሎም ይሞታል፡፡

  በሰው ልጅ የዕድገት ደረጃ ውስጥ ህጻንነት፣ ታዳጊነት፣ ወጣትነት፣ ጎልማሳነትና አረጋዊነት ደግሞ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ በዕድሜ ወሰን ውስጥ ያሉ ሂደቶች በራሳቸው ከመረዳት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡ አንደኛው የዕድሜ ክልል ከሌላኛው ጋር ካሉት ዐቢይ ልዩነት አንዱና ዋነኛው የመረዳት ኹነት ነው፡፡ ይህ መረዳት በራሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየበለጸገ አልያም እያነሰና እየደበዘዘ ይሄዳል፡፡

  አንድ ሰው በነጠላ፣ በቡድንም ኾነ እንደሕዝብ የመረዳት አቅሙ የሚወሰነው ትላንት ካሳለፈው ሂደት፣ ካለበት ነባራዊ ኹኔታና ለወደፊት መኾን ከሚፈልገው ኹለንተናዊ ኹኔታዎች አንጻር ብቻ ሳይኾን ውስጣዊና ውጫዊ ገፊ ምክንያቶችንም አብሮ የሚይዝ ነው፡፡

   ለአብነት፡- ስለአንድ ሀገር ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታዎች በቂ መረዳት ያላቸው ሰዎች በአብዛኛው ታሪካዊና ወቅታዊ ኹነቶችን የሚከታተሉ ብቻ ሳይኾኑ በቂ አስተማማኝና ጥሬ ሃቆችን የያዙ መረጃዎችም የሚደርሷቸው ሊኾኑ ግድ ይላቸዋል፡፡ ከራሳቸው ኹለንተናዊ ትጋት ባሻገር የኾኑ ነገሮች እንዳሉ መረዳትና መገንዘብን ይጠይቃል፡፡   

  በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜና መረዳት – መረዳትና ጊዜ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ያሉ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው፡፡

   ኾኖም በመረዳትና በጊዜ መሐከል ከሰው አንጻር ስንመለከት፡-

1ኛ. አንዳንዱ ነገሮች ከመኾናቸው በፊት የሚገባው አለ፤

  • የነገሮችን ሂደት ትርጉም ባለው መንገድ እየፈተሸ የመጣና በዛም ላይ ልምድ ያለው አካል፤
  • መኾን ያለባቸውን፣ እየኾኑ ያሉና በመሐከላቸው ስላሉ ክፍተቶች በበቂ ኹኔታዎች የዳበረ ስጦታና ክህሎት ያለው ሰው፤
  • ከመሣሪያዎች (Means) ተነሥቶ ፍጻሜ (End) ከመድረሱ በፊት ይረዳል፤ 

2ኛ. አንዳንዱ ነገሮች ሊኾኑ ሲቃረቡ 11ኛው ሰዓት ላይ ይገባዋል፤

  • እነዚህ ምንም እንኳ የነገሮች ሂደት እንደመጀመሪያዎቹ ባይገለጥላቸው – በሂደት በሚመለከቷቸው ፍንጮችና መገለጫዎች በመነሳት ከረፈደም ቢኾን የሚገለጥላቸው ናቸው፡፡

3ኛ. አንዳንዱ ነገሮች ሲኾኑ – በኾኑበት ቅጽበት ይገባዋል፤

  • እነዚህ ልክ ነገሩ ሲከሰት ከፍጻሜው (End) ተነሥተው – መሣሪያዎቹን (Means) የሚተነትኑ ናቸው፡፡

4ኛ. አንዳንዱ ነገሮች ከኾኑ በኃላ ይገባዋል፤

  • እነዚህ ነገሩ ተከስቶ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ተጽዕኖው በአደባባይ ከታየ በኃላ የሚረዱና የሚገነዘቡ ናቸው፡፡

5ኛ. አንዳንድ ሰው ነገሮች ኾነውም ላይገባው ይችላል፤

  • አንዳንዶች ደግሞ ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዕይታዎች የተነሣ ነገሮች ኾነውም እንኳ ማየት የሚፈልጉትን ብቻ ከማየት፤ መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ከመስማት የተነሣ በራሳቸው ዛቢያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡

  የዓለም ታሪክ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ግለሰቦች፣ ቡድኖችም ኾኑ ሕዝብ እጅግ ጥቂቶች ከ1 እስከ 3 ባሉት ውስጥ ሲኾኑ አብዝሃዎች ግን ከ4 እስከ 5 ባለው ውስጥ መኾናቸውን ነው፡፡

  በመረዳትና በጊዜ መሐከል ያለውን ግንኙነት እጅግ አስፍቶና ተንትኖ ማየቱ እጅግ ከሚያስፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ቀድመው የተረዱ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 3 ያሉ ጥቂቶች – ከተራ ቁጥር 4 እስከ 5 ያሉ እጅግ አብዝሃዎች እስኪረዱ ድረስ የሚከፍሉት ኹለንተናዊ መስዋዕትነት ቃላት ከሚገልጹት በላይ መኾኑ እጅጉን የሚያሳምም መኾኑ ነው፡፡

   የዓለም ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ እንደዚህ መለያየት በነጠላ ካለው ተጽዕኖ ይልቅ በጋራ ለጋራ ስለጋራ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽዕኖው እጅግ ከፍተኛ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ አንዳንዱ ስለሀገር ሲል የራሱን ኹለንተናዊ ፍላጎት ጭምር ለመስዋዕትነት ያቀርባል፤ አንዳንዱ ስለራሱ ኹለንተናዊ ፍላጎት ሲል ሀገሩን ኹለንተናዊ መስዋዕትነት ያስከፍላል፤ አንዳንዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ሀገሩና ሀገሩ ብቻ ትኾናለች፤ አንዳንዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ራሱና የራሱ ጉዳይ ብቻ ይኾናል፤

  አንዳንዱ ስለሀገሩ እንቅልፉን ያጣል፣ ይናደዳል ብሎም ይቆጫል፤ አንዳንዱ ስለሀገሩ ግድ የማይሰጠው ይኾናል፡፡ ኢትዮጵያዊ ኾኖ ስለኢትዮጵያ የሚያስብ ብዙ እንዳለ ኹሉ አንድ ኬንያዊ ኢትዮጵያን እንደሚያያት የማያይ ኢትዮጵያዊም ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡

   የመረዳትና የጊዜ ጉዳይ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የሀገር ጉዳይ የጋራ እስከኾነ ድረስ ጥቂቶች ሳይኾን አብዝሃዎች ይሳተፉ ዘንድ ይጠበቃል፡፡ ኾኖም በተግባር የሀገርን ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታ የሚወስኑት ጥቂቶች ብቻ ሳይኾን እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡

  ብዙዎች በአንደበታቸው ስለአብዝሃ ተሳታፊነትና ስለሕዝብ ኃያልነት በአደባባይ ብዙ ብዙ በጣም ብዙ ይደሰኩራሉ፡፡ ነገር ግን በተግባር የአብዝሃ ተሳታፊነት ከወሬ አልዘለለም – ሕዝብም መነገጃ ከመኾን አለመዳኑን አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

   ለዚህም ዓለምና የዓለም ታሪክ ብዙ ነገር ያሳያል፡፡ ከነዛ ውስጥ አንዱና ዋነኛው የመረዳትና የጊዜ ጉዳይ ከላይ በአምስት ከፍለን እንደተመለከትነው የተለያየ ከመኾኑ የተነሣ አስመሳዮች እንደግልጸኛ፣ ሀሰተኞች እንደእውነተኛ፣ ጨካኞች እንደየዋህ፣ ሀገር ሻጮች እንደሀገር ወዳድ፤ ሴረኞች እንደጠቢብ፣ ዘቃጮች እንደከፍተኞች፣ ተዋራጆች እንደተከባሪዎች፣ ባዶዎች እንደተሞይዎች፣ ገዥዎች እንደመሪዎች፣ አሽከሮች እንደጌቶች፣ ባሪያዎች እንደነጻዎች፣ ወረኞች እንደአዋቂዎች፣ አላዋቂዎች እንደሊህቆች፣ ከሃዲዎች እንደአማኞች፣ የጥላቻ ባለቤቶች እንደፍቅር ባለቤቶች፣ ስይጥኖች እንደሥልጥኖች፣ ቂመኞች እንደይቅር ባዮች  – – – ወዘተ የታዩበትና የተቆጠሩበት ጊዜ በዓለም ታሪክ በርካታ ነው፡፡

   በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ የዓለም ታሪክ የሚያሳየን ትልቅ ዕውነት ቢኖር ብዙዎች ነገሮችን የሚረዱት እጅግ ዘግይተውና እጅግ በጣም አርፍደው ከመኾኑ የተነሣ የሀሰተኞች፣ የአጭበርባሪዎች፣ የሴረኞች፣ የከሃዲዎች፣ የስይጥኖች፣ የባዶዎችና የዝቃጮች መጫዎቻ ኾነዋል፡፡

  መጫወቻነቱ በአብዛኛው ከተጫዋቹ የሚመነጭ ቢኾንም ቅሉ – ለመጫወቻነት ራሱን ያዘጋጀውም አካል ቢኾን ሚናው የላቀ ነው፡፡ ብዙዎች ሀሰተኞች አብዝተው ስለእውነት ያወራሉ፤ በርካታ በቅኝ ግዛት ውስጥ የቅኝ ገዥዎች ባሪያና አሽከር የኾኑ ገዥዎች እጅጉን አብዝተው ቀን ከለሊት ሕዝቡን ለማደንዘዝ ስለሀገር ፍቅርና ብሔርተኝነት ይደሰኩራሉ፤ ብዙዎች በአስመሳይነት በሀገርና በሕዝብ ስም ፍሬ ከርስኪ ትርጉም አልባ ዲስኩሮችን ይለፈልፋሉ፤

   ብዙዎች እልም ያሉ አስመሳዮችና ሴረኞች ኾነው ስለግልጽነትና ሕብረት አብዝተው ይጮሃሉ፤ ብዙዎች ሕልውናቸው በመሰይጠንና በጠላትነት ላይ ኾኖ እጅጉን እስኪሰለች ድረስ ስለሥልጣኔና ስለፍቅር ያወራሉ፤ ብዙዎች እልም ያሉ ትያትረኞችና አቅመ ቢሶች ኾነው ስለአቅምና ብቃት ሲያወሩ ትንሽ እንኳ አያፍሩም፤ በተደጋጋሚ ይዋሻሉ – በተደጋጋሚ ቃል ይገባሉ ግን አይፈጽሙም – ትርጉም ያለው የረባ አንዳች ሥራ የላቸውም ነገር ግን ብዙዎች ነገሩ የሚገባቸው እጅግ ዘግይቶ በመኾኑ ብዙዎች በደመ ነፍስ ይከተላቸዋል፡፡ እነሱ አስበው፣ አውጥተውና አውርደው ይጫወታሉ – ሌላው ሳያስበው፣ ሳያወጣና ሳያወርድ ብሎም ሳያገናዝብ የነሱ መጫወቻ ይኾናል፡፡

   ሌባ ሊሰርቅ ሲል ቢያንስ ቢያንስ ሊያዋጣኝ ይችላል ያለውን ስልት ይጠቀማል፡፡ ስልቱ ይሰራል ወይስ አይሰራም፤ ይያዛል ወይስ አይያዝም – የሚለው ከዛ በኃላ የሚመጣበት ነው፡፡

   ማንም ቢኾን እሰርቅሃለው እያለ አይሰርቅም – አልሰርቅም እያለ ግን ይሰርቃል፤ ማንም ሀገሬን አልወድም እያለ ሀገሩን አይጎዳም – ሀገሬን አፈቅራለውና መስዋዕትነት እከፍላለው እያለ ግን ሀገሩን ለጠላት አሳልፎ ይሸጣል፤ እታመናለሁ እያለ የሚክድ እንጂ እክዳለው ብሎ በአደባባይ እየዞረ የሚክድ የለም፤ አብሬ አለው አለሁ እያለ – የውስጡን በውስጡ ይዞ እንደመዥገር በአካላት ላይ ተጣብቆ – ቆይቶ – ምቹ ኹኔታ ሲያገኝ ደግሞ ፈንግሎ የሚጥል እንጂ መዥገር ነኝ እያለ የመዥገርነት ሥራ የሚሰራ ከወዴት ይገኛል? አቅም አልባ ቦዶ እንኳ ቢኾን አቅም አለኝ ብሎ የአቅም አልባነት ሥራ ይሰራል እንጂ ራሱን እያዋረደ የሚሰራ ከቶ አይገኝም፡፡

  ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚኾነው በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ ሀገራት ገዥዎች እልም ያሉ የቅኝ ገዥዎች አሽከር፣ ባሪያና ተላላኪ ገረዶች ኾነው ሳለ በአደባባይ ራሳቸውን እ-ላይ ሰቅለው ስለሀገር ፍቅር ፍሬ ከርስኪ ትርጉም አልባ ነገሮችን የሚያወሩ ገዥዎች እልፍ አላፍ እንደነበሩ፤ አቅመ ቢሶችና ሀሰተኞች ሳሉ እጅጉን አብዝተው የጌቶቻቸውን መልካም ፍቃድ ብቻ እየተከተሉ ስለሀገር እየማሉና እየተገዘቱ ሀገራትን እንደበዘበዙና እንደሸጡ እስከዛሬ ድረስም የቅኝ ገዥዎች አሉታዊ ገጽታ እንዳይጠፋ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ታሪካቸውና የሀገራቱ ሕዝብ ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታ ማሳያ መኾኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

    የሰው ልጅ ነገሮችን የመረዳት አቅምና ብቃት ባሕሪያዊና ጠባያዊ ልዩነቶች ያሉትና ሊኖሩት የሚችሉ በመኾኑ ፍጹም ተመሳሳይ መረዳት ላይ በተመሳሳይ ጊዜና በተመሳሳይ ኹኔታ ላይ አብዝሃ ይደርሳል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ቢኾንም ቢያንስ በተቀራራቢ ጊዜና ባለመረዳት የሚመጣ አሉታዊ ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ቢኾን መልካም ይኾል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply