“አንበሣን ፈርቼ ዛፍ ላይ ብወጣ ነብር ጠበቀኝ” – ነገረ አማራ (ግርማ በላይ)

ዕድለቢሱ አማራ አሁንም በአዲሱ መንግሥት ከሥራና ከመኖሪያ እየተፈናቀለ እንደሆነ ከሚሰሙ እጅግ በርካታ  ሮሮዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ይቺ “ተራው የኛ ነው!” የሚሏት ወያኔያዊ ፈሊጥ የኢትዮጵያን ኅልውና ክፉኛ እየተፈታተነች ትገኛለች፡፡ የወያኔን የውድቀት መንስዔ ያላወቁና ማወቅ ያልፈለጉ አንዳንድ ወገኖች “ኢትዮጵያን የሚጠብቅ ኃይል የለም”  ወይም ቢኖርም “የኔው ወገን ነው” ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመነሣት የወያኔን ድርጊት በኮፒ-ፔስት እንዳለች ገልብጠው በባሰ ደረጃ በተግባር እያሳዩ ናቸው፡፡ ሃይ ባይ ደግሞ የላቸውም፡፡ “ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” መባሉ እንግዲህ ለዚህ ነው፡፡ መቆየት ብዙ ያሳያል፡፡ አሁን አዲስ አበባ ላይ እየተስተዋለ ያለው የዘረኝነት አዙሪት እግዚዖ የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገረ ሥራችን ሁሉ ከድጡ ወደ ማጡና “አልሸሹም ዘወር አሉ” እንዲሉ ነው፡፡

ከወለጋ አካባቢ እንዲህ ሰማሁ፡፡ አንዲት ገጠመኝ ናት፤ ግን ብዙ ሀገራዊ ነገር ትጠቁማለች፡፡ ቅርጽና ይዘቱን እየለዋወጠ የሚያምሰን ወያኔነት አንድ ቦታ ካልቆመ እጅግ አደገኛ መሆኑንም ታሳያለች፡፡ ልብ ብላችሁ እዩልኝ!

አንዱ በ“ኢትዮጵያ” ንግድ ባንክ ይሠራል – ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” ያደረግሁበት ምክንያት በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማንም ሥልጣን የሚይዝ ዘረኛ ሁሉ እንደግል ሀብት ይዞ የሚያልባት የአንድ ወገን የግል ሀብት እየሆነች መምጣቷን ለመጠቆም  ነው – “ሥልጣን የሚይዝ” ስል በግድ አንዱንና ጫፍ ላይ ያለውን ሰው ማለቴ እንዳልሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ፃዲቅና መልኣክ ቢሆን ከታች እስከላይ የተኮለኮሉት እርሱን ካልተከተሉ ትርፉ ድካም ነው – ይህም ነው በሀገራችን አሁን እየሆነ ያለው፡፡ አንድ እጅ አጨብጭቦ ዘፈንን አያደምቅም፤ አንድ እንጨት ነዶም ወጪት አያወጣም፡፡ እንጂ ልጁ ጎበዝ ነበር፡፡ የከበቡት ግን ከገማው በርሜል የሚቀዱ በመሆናቸው አላላወሱትም፡፡ ደፈር ሊል ደግሞ አልቻለም፡፡ በዚህ የሰቀቀን አካሄዱ ወዴት ሊያደርሰን እንደሚችል መገመት ያስቸግራል፡፡ የበሰበሰና በዘረኝነት አባዜ የተግማማ ቤት ውስጥ አንድ ብልቃጥ ሽቶ ብዙም ዋጋ የለውም፡፡ ለማንኛውም እግዜር ይሁነን፡፡

… ያን ሰው የአካባቢ ባለሥልጣናት ከህግ አግባብ ውጪ ገንዘብ ለማውጣት ፊርማህን ‹እዚህች ላይ ፈርምልን› ይሉታል፡፡ ተመልከቱ፡፡ አንዱ ጨቡዴ ሲሄድ ሌላው የባሰበት የለዬለት መደዴ ጨቡዴ መተካቱ ነው፡፡ ሰውዬው ‹ህገ ወጥ ሥራ አልሠራም› ይላቸዋል፡፡ ያሰቃዩትና ወደ ማዕከል ሄዶ ሪፖርት እንዲያደርግ ይነግሩታል – በጎሣው ምክንያት ክፉኛ እያበሻቀጡ (ቀን አይጉደልብህ አንተዬ!)፡፡ የፈለጉትንም ገንዘብ በፈለጉት መንገድ አውጥተው እንደፈለጉ ያደርጉታል፡፡ ይገርማል፤ ልክ እንደወያኔዎቹ ሁሉ ለአምስትና ለአሥር ይደራጁላችሁና ከባንክ የፈለጉትን መጠን ብድር ይጠይቃሉ፤ በሚያስቀምጧቸው አዲስ ፈረሶችም ብድሩ እንዲፈቀድ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልክ የሀገሪቱ ገንዘብ በአዲሶቹ የጎሣ ገዢዎች ከላይ እስከታች እየተመዘበረ ነው – ነገሩ “እኛስ ለምን ይቅርብን” ዓይነት መሆኑ ነው – ነገር ካለቀ በኋላ በስተመጨረሻ መባነናቸው ነው፡፡ ግን የነዚህ ደግሞ ከመጀመሪያዎቹም ባሰ፡፡ እነዚያ ቢያንስ ጥቂት ዓመታትን ታግሰው ቀስ በቀስ ተለማምደው ነው ወደ ምዝበራው የተዘፈቁት፤ ሰውን ወደ ማሰቃየት ወንጀሉም የተነከሩት፡፡ እነኚህ ግን የፋራነታቸው ብዛት ገና በሰባትና በስምንት ወር ውስጥ ሥልጣኑንም ገንዘቡንም ለመቆጣጠር ያደረጉትና እያደረጉት ያለው ነውረኛ አካሄድና የተቻኮለ የሚመስል ድርጊት ከአሁኑ ዐይን ውስጥ እያስገባቸው ነው – የሰው ዐይን ደግሞ ድንጋይ ይሰብራልና አይዘልቁበትም፡፡ ሌባ ሲባል፣ ዘረኛ ሲባል፣ ጎጠኛ ሲባል፣ ማይም ሲባል ሀፍረትና ይሉኝታ እንደሌለው አሁን ገና ይገባን ጀምሯል፡፡ በሽታ እንጂ ዘረኝነትና እርሱን ተመርኩዞ የሚደረግ ዝርፊያና ውንብድና በተጋቦት የሚተላለፍ አይመስለኝም ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ የወያኔ ዘመን ድርጊቶች በተለይ የገንዘብና የመሬት ዘረፋው በአሁኑ ተረኞችም እጅግ ተባብሶ ቀጥሏል – ለካንስ ወያኔዎች ወደው አልነበረምና እንደዚያ በገንዘብና በመሬት ፍቅር የታወሩት! ውይ፣ ለካንም መጥፎ በሽታ ኖሯልና! ከዐድዋ መጠራራቱ ለጊዜው ጋብ ብሎ ከወለጋ መጠራራቱ ተተክቷል፡፡ የሚገርም የታሪክ ምፀት፤ አስደናቂ የሁኔታዎች መመሳሰል፤ አስደማሚ የደናቁርት መተካካት፡፡ የትዕቢታቸው መወራረስም እንዲሁ የሚገርም ነው፡፡ ከነሱ ሌላ ሌላው ሰው አይመስላቸውም፡፡ ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለችና ከነዚህ ራሳቸውን ዕንቁ ካደረጉ ወንድሞቻችን ብዙ የምናማረው ነገር አለ፡፡ ብልኆች ከውድቀታቸው ብቻ ሣይሆን ሲታዩ የቆሙ ከሚመስሉ እንደ እውነቱ ግን ቆመው ከወደቁም ጭምር ይማራሉ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ይህን እውነት ስንናገር ደግሞ አንዳንዶች – ማለትም – “ተው የኔን እግር እየበላ ነው”ባዮች ይቃወሙናል፡፡ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ተቃዋሚዎችና የነሱ ልሣናት ይህን ሁሉ በሀገር ላይ እየደረሰ ያለ ግፍና በደል አውቀው እንዳላወቁ በመምሰል  ሃቁን ሸፋፍነው የሚያደርጉት የመሞዳሞድ ጥረት እጅግ ይገርማል፤ ያስተዛዝባልም፡፡ እነሱና የነሱ የሆነ ኃይል ወደ ሥልጣን ቢጠጋ ምን ሊከሰት እንደሚችል ገና ከሩቁ እያሸተትን ነው፡፡ ሀገሪቱ የምታመርተው ፖለቲከኛ በአብዛኛው ውሸታምና አስመሳይ ከመሆን ሊዘል አልቻለም፤ ይህስ እውነትም መረገም ነው፡፡ እነሐጎስ ያደረጉትን እንደበዳዳ ሲያደርጉት ነውር ካልሆነ ማንም ቢያደርገው ግዴላቸውም ማለት ነው፡፡ ችግራቸው አንግዲያውስ ተራቸው ቶሎ አለመድረሱ ነው፡፡ ችግራቸው “ሕዝቡን አቶ ‹ኤክስ› ከሚያሰቃየው አቶ ‹ዋይ› ቢያሰቃየው ይሻላል” ከሚል እንጂ እውነተኛ የሕዝብ ብሶትና በደል ይሰማቸዋል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ትላልቅ ስምና ዝና ያላቸው ድርጅቶችና ንቅናቄዎች ሳይቀሩ ይህን ሀገራዊ እውነታ እየተረዱ ከህዝብ ብሶት ይልቅ ለባለውለታነት ስሜት ተሸንፈው አድርባይ መሆናቸው በግልጽ እየታዬ ነው፡፡ በወያኔ ሠፈር የምትታይን እያንዳንዷን ህፀፅ ሲያወጡና ሲያወግዙ የነበሩ ትልልቆች ዛሬ ተረኛውን ወገን ምን እየሠራ እንደሆነ እዚሁ አጠገቡ ሆነው እየታዘቡ ትንፍሽ አይሉም፡፡ ሌሎች ሲናገሩ እንኳን ሌላ በተናገረው እነሱን ይሰቀጥጣቸዋል – ለለውጡ ካላቸው ከፍተኛ አክብሮትና አመኔታ የተነሣ – ጥሩ ነው፡፡ ወደዚህ አስተዛዛቢ ደረጃ የወረዱት ምናልባት ትግል ሰልችቷቸው ሊሆን ይችላል፤ የዕድሜ መግፋት አስቸግሯቸው ሊሆን ይችላል፤ ተስፋ መቁረጥ ተፅዕኖ አድርጎባቸው ሊሆን ይችላል፤ ማን ያውቃል የገንዘብ ጉርሻና የሥልጣን ተስፋ ጥላቸውን ጥለውባቸው ሊሆንም ይችላል፤ በትግል እርዝማኔ ተሰላችተው ሊሆን ይችላል፤ የሕዝብ ተቀባይነት እየሣሣ መጥቶ ከሆነ በርሱም ተስፋ ቆርጠው ሊሆን ይችላል … ፡፡ ነገር ግን ተነሳንለት ያሉት እውነት በጠራራ ፀሐይ ሲደፈጠጥ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን እንዲህ ፀጥ-ረጭ ማለት አነሳሳቸውን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡ ደግም አይፈረድብንም፡፡ በአንድ ራስ ሁለት ራስ ማየት የለብንምና፡፡  እንጂ … ቆይማ ወደተነሳሁበት ልመለስ፡፡ በተሳሳተ መስመር ገብቼ ጠፋሁ መሰለኝ፡፡

ያ ሰው ፊንፊኔ መጥቶ ለበላይ እንዲያመለክት በተነገረው መሠረት አዲስ አበባ መጥቶ በዘር ሐረጉ ምክንያት የደረሰበትን ሁሉ ለሪጂን ኃላፊው አንድ በአንድ ይነግረዋል፡፡ የተመለሰለት ግን እርሱን ብቻ ሣይሆን መላ አማራን የሚያስደነግጥ ነው፡፡ በድርበቡ ልንገራችሁ – “ስማ አንት ነፍጠኛ – በኛ አካባቢ ዱሮ አንድም ሌባ አልነበረም፡፡ ልብስ ተሰጥቶ ባለቤት ባይሰበስብ ከዓመት በላይ ይቀመጣል፡፡ እናንተ ስትመጡ ግን ሌብነት መጣ፡፡ …. ውሸትህን አትቆልልብኝ፡፡ ምንም በደል አልደረሰብህም፤ ደውለው ነግረውኛል፡፡ ሥራውን ካልፈለግህ መልቀቂያ አስገባ፡፡…”

ሁሉንም መናገር አልፈልግም፡፡ ይህንንም የተናገርኩት አማራው ማወቅ ስላለበት ነው፡፡ እውነትን ሸፋፍነን መሄድ ዋጋ ያስከፍላልና አማሮች ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ለብቀላና ለክፋት ግን እጅ መስጠት የለባቸውም፡፡ ሁሉም የማታ ማታ የሥራውን ያገኛልና ቀን ሰጠን ብለው እንደሚጃጃሉት ወገኖቻችን መሆን ለበለጠ ቅጣት ሆን ብሎ እንደመዘጋጀት ነው፡፡ በየቦታው አማራ ችግር እየደረሰበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከራሱ ወገኖች ሳይቀር በሚወረወርበት ጦር የሚጎዳ አማራ ብቻ ነው፡፡ የአማራ ማኅጸን እባብም፣ ዘንዶም፣ ጅብም፣ እስስትም፣ … እየፈጠረ አማራውን ማስፈጀቱ ከጥንትም የነበረ ነው፡፡ ዕርግብና እባብን የሚፈጥረው የአማራ ማኅጸን ዳኛቸው አሰፋንና ገነት ዘውዴን በአንድ ወይ በተቀራራቢ ማኅጸኖች ፈጥሯል፡፡

እደግመዋለሁ፡፡ አማሮች ተጠንቀቁ፡፡ ቀኒቱ ብትቀርብም በአንዲት ደቂቃም ውስጥ ብዙ ጉዳት ይደርሳልና  መጨረሻችሁ ያማረ እንዲሆን ከጠላቶቻችሁ ወጥመድ ተጠበቁ፡፡ አሁን ሀገር እንደሌለው ፍልስጥኤም ናችሁ፡፡ ለብሳችሁ እንዳያምርባችሁ፣ አግኝታችሁ እንዳትወዙ፣ ተናግራችሁ እንዳትደመጡ፣ ተሹማችሁ እንዳትደምቁ፣ … በገዛ ሀገራችሁ በገዛ ወንድሞቻችሁ በገዛ ልጆቻችሁ አፍዝ አደንግዝ ተዙሮባችኋልና አበቅቴው እስኪሽር፣ መርዙ እስኪረክስ፣ የድግምቱ ጊዜ እስኪያልፍበትና እስኪመክን… ከክፋት ርቃችሁ አባቶችና እናቶች በርትታችሁ ጸልዩ፤ ወጣቶች ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ራሳችሁንና አካባቢያችሁን ጠብቁ፡፡ በናንተ ላይ ያልተነሣ ጠላት የለም፡፡ ሳትለያዩ በኅብረት የሀገራችሁን ትንሣዔ ለማብሰር ከሚመጣ ጤናማ ኃይል ጋር ታግላችሁ ኅልውናችሁን አስጠብቁ፡፡

የከዳቻችሁ ሀገር ነገ ፊቷን ወደ እናንተ ስታዞር ሁሉም ነገር ይስተካከላልና በዚህ በአሁኑ የጨረባ ተዝካር የሚመስል የዕብዶች ድራማ አትደነቁ፡፡ …. ሁሉም ማለፉ በጄ እንጂ … ቀድሞም መነገሩ አጽናናን እንጂ አንዳንድ ነገሮች በርግጥም ኅሊናን ከማቁሰል ባለፈ ብዙ ጉዳት ማስከተል በቻሉ ነበር፡፡ “ከላይ ነው ትዛዙ” ይላሉ የታክሲ ላይ ጽሑፎች፡፡ እውነት ነው!

ሰላም ለኢትዮጵያ!

Leave a Reply