ኢትዮጵያን ማፍረሱ ለምን ከባድ እንደሆነ በደምብ ገባኝ! ወያኔና መሰሎቹ ተስፋ ቁረጡ!…ነፃነት ዘለቀ

እውነቴን ነው – እኔ ራሴም “ኢትዮጵያውያን እንዲህ እየተናቆርን ከምንኖር ለምን ተለያይተን አንክሞረውም?” ወደሚል የግል ድምዳሜ ደርሼ ነበር፡፡ ይሁንና ያለፉት እሁድና ቅዳሜ ያመላከቱኝ ነገር ሌላና የማልጠብቀው ሆኖ አገኘሁት፡፡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከጥንት ጀምሮ ቀና ደፋ የሚሉ ወገኖች እነሱ ራሳቸው በተደጋጋሚ ሞክረው ቢያቅታቸው የገዛ ወገኖቻችንን በሤራ መረባቸው እየጠለፉ እኛኑ በኛው ላይ ቢያሰልፉብንና በጊዜው አገላለጽ በሆድ የሚያስቡ የቀን ጅቦችን በየዘመናቱ ቢያሠማሩብንም እኛ ግን እስካሁን አልፈረስንም፤ ወደፊትም አንፈርስም፡፡ በመለስ ዱካ ደብረፅዮን ቢተካም፣ ነገ ደግሞ በዳውድ እግር ሌላ ቢቆምም ኢትዮጵያ ግን እየተንገዳገደችም ቢሆን መኖሯን ትቀጥላለች፤ ከእግዲህም ቢሆን መቼም አትበታተንም፡፡ የኔም ምኞት፣ ያንተም ሥጋት፣ የነሱም ፍርሃት… ሚዛን የማይደፋ እንደሆነና ከወቅታዊ ትርምስ ከመፍጠር ውጭ  የኢትዮጵያን ቋሚ ምሠሦዎች ሊያናጋ የሚችል ነገር እንደሌለ አንድ ኅያው ምሣሌ ባይኔ በብረቱ ተመልክቼ ተደንቄያለሁ፡፡ ስለዚህ ተስፋ አለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔና መሰል የመከራ ድግስ ደጋሾች ሁሉ ተስፋ ሊቆርጡ ይገባቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የግፍና በደል ኮማሪ ወር-ተረኞች ሊደንግጡ፣ ተስፋም ቆርጠው ከእስካሁኑ በከፋ ደረጃ ሳንጎዳዳ  ጥጋቸውን ሊይዙ የግድና ታሪካዊም ነው ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው . ሟች ይዞ መሞቱን መዘንጋት የዋህነት ነው፡፡ …

ቅዳሜና እሁድ – ጥር 4 እና 5 / 2011ዓ.ም ሦስት ሠርጎችን ታድሜ ነበር፡፡ አንዱ ቅዳሜ ማታ ሁለቱ ደግሞ እሁድ በተመሳሳይ ሰዓት፡፡ (የሚገርማችሁ ሬሣን ቶሎ ለመቅበር ስንቸኩል ሠርግ ላይ ግን ሰዓት ባለማክር ሰውን እናንቆራጥጣለን፡፡ ለዘጠኝ ሰዓት ቀብር ሬሣ በሰባት ሰዓት ከቤት ሲወጣ ለሰባት ሰዓት ሠርግ ሙሽራ ዘጠኝ ሰዓት ይደርሳል – ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ፡፡ አንዱ ለመገላገል – ሌላኛው በሰዎች እንግልት ደስታን ለመሸመት – የሚገርሙ አጋጣሚዎች፡፡)

የቅሜዳው መቼስ ሠርግ አይምሰላችሁ፡፡ ትዝብቴን ለመግለጽ እንጅ አንዱን ከሌላው እያነጻጸርኩ ወይም ፍርድ እየሰጠሁ አይደለምና ፀጉር ሰንጣቂዎች ትንሽ ዕረፍት ቢጤ ውሰዱልኝ፡፡ በመሠረቱ ሁሉም ነገር አንድ ይሁን አይባልም፤ እንዲያ ቢሆን ኖሮ ደግሞ ሕይወት ትርጉም አልባ ናት፡፡ የቀይ ድምቀት በጥቁር ኅልውና ላይ ይመሠረታል፡፡ ረጂምን ካለአጭር ጭራሹን አናውቀውም፡፡ ትልቅ ባይኖር ትንሽ የለም፡፡ በሠንጋ የተደገሰ ድግስ በሙክት የተደገሰን ድግስ ካላከበረ ሠንጋውን ከሰረ፡፡ ትንሽም ብትሆን ልዩነት የሕይወትና የዕድገት መሠረት እንጂ ለጉራና ለትዕቢት የሚዳርግ የዕቡያን የትምክህት ጦር መሆን የለበትም፡፡… በዚያ ሠርግ የመብል መጠጡ ነገር አይነሣ፡፡ ታዳሚዎች ከ600 ቢበልጡ እንጂ አያንሱም፡፡ የተበላው ተበልቶ፣ የተጠጣውም ተጠጥቶ በሠርጉ መጨረሻ የተረፈው የቁርጥ ሥጋ ራሱ በቄራ መኪና ነው የተወሰደው፡፡ ከሠረጉ አይቀር እንደዚያ ነው፡፡ የምትጠራውን ሕዝብ ከድግስህ ጋር አጣጥመህ ከጠራህ አትታማም፡፡ ስትደግስ ደግሞ ሁሉም አይቅርብኝ ብለህና ሁሉንም ነገር ፈልገህ ሳይሆን ሁለንተናዊ አቅምህንና ወቅቱን አገናዝበህ ሊሆን ይገባል – እንደቤትህ እንጂ እንደጎረቤትህ ልሁን ካልክ ትጠፋለህ፡፡ ለአብነት 50 ሰው በሚያምነሸንሽ ድግስ 500 ሰው ብትጠራ ፍላጎትህና ዝግጅትህ አልተጣጣሙምና ከሰው ጋር ትቀያየማለህ፤ በግብዝነትም ትታማለህ፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ ብዙ ጊዜ ብዙ ነገር ስለታዘብኩ ነው እንዲህ የምለው፡፡ ተሰልፈን ውለን ጥርግራጊ ጎመን ላይ የምንደርስበት ሠርግ አይሉት ዐርባ ያጋጥማል፡፡ ደግሞም አንዲት ብርጭቆ ጠላ ወይም ድራፍት ብቻ የምትደርስህ ሠርግም አለ – ሊያውም በዘመድና የሚያውቅህን ከሩቅ አይተህ እጅህን እንደባንዲራ አሥሬ አውለብልበህ፡፡ “ይህም ይታሰብበት” ለማለት የደነቀርኩት የእግረ መንገድ መልእክት ነው፡፡ ይህን ለምን እዚህ ገለጽኩ ግን? የሆዳም ነገር…. “ሆዳም ሰው  አይጠድቅም” የሚባለው እውነት ነው፡፡

… ተጋቢዎቹ የአማራና ኦሮሞ ዝርያ ናቸው – በዘመኑ የወያኔ ቋንቋ፡፡ ወያኔዎች ይህን ባይፈቅዱም እኛ ግን ህግ እየጣስን እንጋባላን፡፡ ዐዋጅ እየሻርን እንዋለዳለን፡፡ ሥርዓት እያፈረስን በጋብቻና በአበ ልጅ እንቆራኛለን፡፡ ጠላቶቻችን እንድንዋጋላቸውና እንድነመነቃቀርላቸው ቀን ከሌት ሲማስኑ እኛ በዚህ መልክ ልፋታቸውን መና እናስቀርባቸዋለን – የኅልውናችን መሠረት ይሄውና ይሄው ብቻ በመሆኑ ቢመር ቢጎመዝዛቸውም ይህን ማኅበራዊ ትስስር መቀጠላችን አይቀርምና ይቅርታ ያድርጉልን፡፡ እስካሁን “ያልተንበረከክነው”ም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የሙሽራው ቤተሰብ – ሁሉም ማለት ይቻላል – በሠፈራችን በጭፈራ አንቱ የተባለ ናቸው፤ በተለይ ሸንኮራኛና ምንጃርኛ፡፡ ይህን የምናውቅ ሠፈርተኞች ጭፈራው እስኪጀመር ሳንቸኩል አልቀረንም፡፡ ሁሉም በጨፈገገበት ዘመን እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ዘና ለማለት ቢጠቀምበት የሚያስፈርድበት አይመስለኝም፡፡ እንጂ እነዚያ የእፉኝት ልጆች ዕድሜያቸው ይጠርና ዘመናችን የልቅሶና የዋይታ፣ የጭንቀትና የጥበት፣ የርሀብና የሽብር … እንጂ የደስታና የሃሤት እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ቢሆንም እንደባህሉ “ዋ ብሎ ጉርስ” አይቀርምና በዚያ ሠርግ ለተወሰነ ጊዜ ታዳሚዎችም ዓለማችንን ቀጨንበት፡፡

ዲጄው የተለያዩ ሙዚቃዎችን ከመነሻው ጀምሮ ይከፍት ጀመር፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ጉራግኛ፣ ደቡብኛ … እየተከታተለ መቅረብ ጀመረ፡፡ የወያኔን ቋሚ ህግ ድባቅ የመቱ የሚመስሉትን ታዳሚዎች ዘወር ወር ብዬ ተመለከትኩ፡፡ በግምባር ምልክት፣ በአለባበስ፣ በፀጉር አሠራር፣ በቋንቋና በአነጋገር ቃና፣ አልፎ አልፎም በፊትና በአካል ቅርጽ … ጥሎብኝ …. የዜጎችን ጎሣዊ ማንነት መገመት እንደቅርብ ጊዜ ልማዴ አድርጌዋለሁና ታዳሚዎችን ስታዘብ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን እንደሚወክሉ ተረዳሁ፡፡ ዘፈኖች ሲከፈቱም ምንም እንኳ ብዙዎች ዳንኪረኞች የሁሉንም እኩል ወይም ብዙም በማይተናነስ ሁኔታ ቢጨፍሩም የትኛው ታዳሚ በየትኛው ይበልጥ ፊቱ እንደሚፈካ ስለሚገባኝ ያ ትልቅ አዳራሽ ኢትዮጵያን እስኪመስለኝ የሕዝብ አንድነትና ትስስር ቁልጭ ብሎ ታየኝ፡፡ በአንድ ሠርግ ይህን ያህል የጠበቀ ግንኙነት ማየት ተዓምር ነው፡፡ አንድ ሠርግ ላይ ደግሞ በየትኛውም ወገን የሚጠሩ ሰዎች ቢያንስ ከሁለት ለአንድኛቸው ቀረቤታና ወዳጅነት እንዳላቸው ግልጥ ነው፡፡ ሁለት ሙሽሮች አንድን ሀገር የማያያዝ ችሎታቸው እንግዲህ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ውስጡን ስንመረምረው ቀላል እንዳይመስልሽ እህቴ፡፡  

ትግርኛ ዘግየት ብላ ነበር፡፡ እጠብቃትም ነበር፡፡ የምጠብቃትም ከወቅቱ የፖለቲካ ንዝረት አኳያ የሕዝቡን አጸፋ ለማየት በመጓጓቴ ነበረ፡፡ ዘፈኒቱ መጣች፡፡ መድረኩ እንደሞላ ነበር፡፡ አንድም ሰው አላቋረጠም፡፡ እንዲያውም በእልህ በሚመስል አኳኋን የዳንኪረኛው ብዛት ጨመረ፡፡ አዲስ ገቢውም የነበረውም ሥልት ለውጦ መጨፈሩን ቀጠለ፡፡ ገረመኝ፡፡ ያ ሁሉ ትንግርት መሰል የወያኔ ግፍና በደል በተሰራጨ ሰሞን እንዲህ ያለ የሕዝብ አንድነት ሲታይ፣ እንዲህ ያለ የፍቅር ትስስር ባልተጠበቀ መልክ እውን ሲሆን ብዙ ነገሮች እውነትም ወያኔ ወለድ አርቲፊሻል የሆኑ ያህል ተሰማኝ፡፡ የኔም አመለካከት በአንዴ ተለወጠ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፉ ክፉውን እየረሳ የደጉን ቀን ትውስትታ እንደሚያዳብር ገባኝ፡፡ “ተዋጋ፣ ተጣላ፣ ተገዳደል…” እያሉ ቢወተዉቱትም መሪዎቹን ቀድሞ የሚሄድ እጅግ አስደናቂ ሕዝብ መሆኑን አስተዋልሁ፡፡ ይህን ሕዝብ መናቅ የመጨረሻ ጅልነት እንደሆነም ገባኝ፡፡ የሚንቁን ግን ሞልተዋል – መጨረሻቸው አያምርም እንጂ፡፡ የሚንቅ እኮ ራሱ የተናቀና ራሱንም በራሱ የሚያዋርድ ነው፡፡

ዘፈኑ ቀለጠ፡፡ ኢትዮጵያም በአንድ ማዕድና በአንድ መድረክ ቀለጠች፡፡ ለሙሽሮች መልካም ትዳርንና የኑሮ መሠረትን በዚህ አጋጣሚ ተመኘሁ፡፡ “መጀመር እንዲህ ቀላል ነው፤ ጨርሱት” ብያለሁ፡፡ ወቅቱ ዘመነ መርዓ እንደመሆኑ በነዚህ ሠርጎች የሚጋቡና ከነሱ የሚወለዱም ሁሉ ለኢትዮጵያችን መድኅን እንዲሆኑ በጋራ እንጸልይ፡፡ የእርጉማን ሽንቶች እየተበራከቱ መጥተው ሀገራችንን ወደውድቀት ጫፍ እድረሰዋታልና በቆፈሩት ጉድጓድ ራሳቸው እንዲገቡበት በዚህ አጋጣሚ እንጸልይ፡፡  

ከእሁዱ ሠርጎች አንደኛው የትግሬ፣ የአማራና የኦሮሞ ቅልቅል ሠርግ ነበር – ዳሪዎቹም ተጋቢዎቹም፡፡ ይገርመኛል፡፡ እኛን ኢትዮጵያውያንን እግዜሩ እንዴት አድርጎ እንደሚሸምነን፣ እንዴት አድርጎ ከቆላ ከደጋ አገናኝቶ እንደሚያጠላልፈን ስመለከት “ከቶ እንደኛ የታደለ ሕዝብ አለ ወይ?” እላለሁ – ጨመት ስል ነው ታዲያ፤ ሳብድ ግን አያድርስ ነው፡፡ እግዜሩን እንዴት እንደምራገም አታንሱት፡፡ “የተረገምን ዕድለኞች ነን” ልበል ይሆን?

በዚያ ውብ ሠርግም አንዴ አማርኛው፣ አንዴ ኦሮምኛው፣ አንዴ ትግርኛው በዲጄው እየተቀያየረ ሲጦቅ ጨፋሪውም ሥልቱን እየለዋወጠ ሲጦቅ ያዬ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ይጠራጠራል፤ ምን ማለታችሁ ነው – በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያውን ለሚከታተል ሰው አማራና ኦሮሞ፤ ኦሮሞና ትግሬ፣ ትግሬና አማራ  በዚህ ዓይነት ድል ያለ ሠርግ መሀል አብሮ መብላትና መጠጣትም ሆነ አብሮ መጨፈር ይቅርና በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩም እኮ አይመስለውም – ሚዲያና እውነታ አንዳንዴ አሁን አሁን ደግሞ ምናልባትም ብዙውን ጊዜ እንደሚለያዩ መገንዘብም ተገቢ ይመስለኛል፤ እንዲህ የምልህ ታዲያ አዲስ አበባ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ስለታዘብኩት ነገር እንጂ ሌላውን አላየሁምና አስዋሽተህ እንዳታስኮንነኝ፡፡ እኛ እንግዲህ እንዲህ ነን – ለማንኛውም፡፡ እነዚያ ሥራ ፈት ፖለቲከኞች ወደነዚህ ቦታዎች መጥተው ቢያዩ ጉዳቸውን ባወቁ ነበር፡፡ ግን ግን የሰይጣን ሽንት የትም ቢገባና ምንም ነገር ቢመለከት ተፈጥሮው አይለወጥምና በድንቁርናቸው መዝለቃቸው እየጎዳን አለን፡፡ እናም እግዜር ይይላቸው፡፡

እንግዲህ ሠርግንና ሀዘንን በመሰሉ ማኅበራዊ ኹነቶች ሕዝባችንን ስናየው አሁንም በአንድነቱ እንደጸና ነው፡፡ “ኦሮሞ ሲሞት አንድም አማራ ቀብሩ ላይ ድርሽ እንዳይል” ተብሎ በነዳውድ ኢብሣ ቢታወጅ እንኳን፣ “ትግሬ ሲሞት አንድም አማራ ዝር እንዳይል” ተብሎ በነአቦይ ስብሃት ቢደነገግም እንኳን ሕዝቡ ግን ዘር ሳይቆጥር እንደውሻ አጥንትና ደም ሳያነፈንፍ ሁሉም ለሁሉም ይሄዳል፤ ይገኛል፤ ያለቅሳል፤ ያዝናል – ከልብ፡፡ በሠርግም አብሮ ይጨፍራል፤ ይጋባል፤ ያጋባል፤ ይዋለዳል፤ ያዋልዳል፡፡ በመከራና በደስታው አንዱ ለሌላው ደጀኑ ነው፤ መከታው ነው፤ ዋስ ጠበቃው ነው፡፡ የተጣላን ለማስማማት በሚደረገው  ሽምግልና፣ በዕድሩ፣ በፅዋ ማኅበሩ፣ በዕቁቡ፣ በፉካው/በሰንበቴው….አብሮ አለ፡፡ አንዳንድ ማፈንገጦች ቢኖሩም ብዙ ሞክረው ስላልተሳካላቸው ተስፋ እየቆረጡ ወደ ብዙኃኑ እየተሳቡ ይገኛሉ፡፡ አፈንጋጭ ደግሞ እንኳንስ በምድር በሰማይም አለ – ሰይጣን በማፈንገጡና ከላይ ወደታች በመጣሉም ነው እኛንም እንዲህ የሚያምሰን፡፡ አይደለም እንዴ? ምቀኛ አታሳጣኝ ነው፡፡ ካወቁበት ምቀኛም የዕድገት በር ከፋች ነው፡፡

ሃይማኖቱ ኖሮ የሃይማኖት መሪዎች ገና ባይፈጠሩም፣  ፖለቲካው ኖሮ የፖለቲካው መሪዎች ገና ባይመጡልንም፣ ሽማግሌዎች ኖረው አመኔታ የሚጣልባቸውና በአርአያነት የምናያቸው ሃቀኛ አዛውንት ባይኖሩንም… እነዚህ ማኅበራዊና ባህላዊ ተቋማት ለሀገር ኅልውናና ለሕዝብ ቁርኝት ያላቸው ፋይዳ ወደር የለውምና በአግባቡ እንጠቀምባቸው፡፡ ከሥጋ ምኞትና ከብልጭልጩ ዓለም ሎሌነት ለመውጣት እየተውተረተራችሁ የምትገኙ የሃይማኖት አባቶች ካላችሁ ከተዘፈቃችሁበት የሥጋ ባርነትና መንግሥታዊ ሆድ አደርነት ወጥታችሁ ሀገርንና ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል ሞክሩ፡፡ በብዙ ነገር ሕዝቡ እንደሚበልጣችሁም ተረዱ፤ ሕዝቡ የሚያከብራችሁ ስለጠመጠማችሁና ሥልጣነ ክህነት ስላላችሁ እንጂ በሥራችሁ እንዳልሆነም ተገንዘቡ፡፡ ሕዝቡ በሁሉም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሣ አንዳች ነገር የሚጠብቀው ከላይ እንጂ ከታች እንዳልሆነ በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ያለመሪ፣ ያለ ሃይማኖት እረኛ፣ ያለ መንግሥት … እንዲሁ ዕውር ድንበሩን በፈጣሪ ኪነ-ጥበባዊ ሥውር ጣልቃ-ገብነት የሚኖር ብቸኛው ሕዝብ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ በተለይ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየታወቀና በአንዳንዶች ዘንድም በድፍረት እየተነገረ ነው፡፡

ይህ ነገር እውነት መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ለምሣሌ በአዲስ አበባ ቀውጢ ቀን ነው – 6/5/2011 ፡፡ ነዳጅ የሚባል አንድም ቦታ የለም – ቢኖርም በድብቅ አስወድዶ ለመሸጥ ይቆለፍበታል – በወገን ችግር ማትረፍ – በዜጎች ስቃይ መክበር ደግሞ እንደጮማ ሥጋ የሚወደድ ዘመን አመጣሽ ባህል ሆኗል፡፡ ይህ የሆነው የአንድ ክልል ወጣቶች መንገድ ስለዘጉ ነው ተብሏል፡፡ ልብ አድርግ – ክፉን ያርቅልንና የሦስት ክልል ወጣቶች ለሦስት ቀናት መንገድ ቢዘጉ እህል አጥተን በርሀብ መሞታችን ነው፤ የአምስት ክልል ወጣቶች ተደራጅተው ጦርነት ቢከፍቱ አንዳችንም በሕይወት ላንተርፍ ነው… ካላቆምነው ተጠየቃዊ ትንቢታዊ መጥፎ ጉዞው በዚህ መልክ ይቀጥላል፡፡ ይህን መሰል አቅም ያለው መንግሥት እንግዲህ ራሱን መመርመር/መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ አሜሪካ ዛሬ በዓለም ነዳጅ ቢጠፋ ለቀጣዮቹ ሃያና ሠላሣ ዓመታት አንዳችም ችግር አይኖርባትም ይባላል፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ቤዛ እንዲሆን በቅድሚያ ራሱ ተስተካክሎ መቆም አለበት፡፡ ከማንና ከነማን ጋርም በትክክል ቀጥ ብሎ ሊቆም እንደሚችል ካላወቀ እንደተወለጋገደ ይሰነባብትና ለአንዱ ዘመን አመጣሽ ማዕበል ተጋልጦ በተራው ወደ ታሪክነት ይለወጣል – ወዳጅ መስሎ አብሮ ያለን ጠላት አስቀድሞ ማወቅ የለየለትን የሩቅ ጠላት ተዋግቶ ለማሸነፍ ያለውን ዕድል በእጅጉ ያሣምረዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግራችን ዋናው ምክንያት- እንደሚመስለኝ – የዕውቀትና የቆራጥነት ጉድለት ነው፡፡ እንደፀጉራም ውሻ አሉ ሲሉን እንዲህ በቀላሉ ሞተን የምንገኝ ከሆን ዱሮውንም አልነበርንም ማለት ነውና ከእያንዳንዱ የዕለት ገጠመኝ ብዙ ተምረን ነገኣችንን የተሻለ ለማድረግ ታጥቀን መነሣት ይገባናል፡፡ ሰው መሳይ በሸንጎ እንደሆንን ዕድሜያችንን መፍጀት የለብንም፡፡ አንድ ቀን መንገድ ቢዘጋ አንዲትም ቀን የምንግደረደርበት ነገር አጣን – ይህ በራሱ ብዙ ያስተምረናል፤ እጅግ ብዙ ያሳስበናልም፡፡ ለመረጃ ያህል ነው፡፡ 

የሰው ዘር የሰው ዘር ነው፡፡ ዐይጥ ወይም ድመት ወይም ሌላ ዐውሬና እንስሳ  አይደለም፡፡ በተለይ በትላልቅ ከተሞች የወያኔና የኦነግ-ሸኔ አስተሳሰቦች የሽባ ሽባ ናቸው፡፡ አብረኸትን አግብቶ ልጆችን አፍርቶ ከባለቤቱ አባት ከባላምባራስ ዳምጠውና ቤተሰቡ ጋር በሰላምና በፍቅር የሚኖረው አቶ ደቻሣ አጠገቡ ያለውን በሪሁንን ትቶ አምስት ኪሎ ሜትር ርቆ ያለውን ገመቹ የሚባል ዘመዱን ለክፉ ጊዜ እንዲደርስለት ማድረግ አይችልም – እንዲያ ለማድረግ ማሰብ ራሱም ዕብደት ነው፡፡ እነፈይሣ ብቻ እንዲቀባበሩ፣ እነስንሻው ብቻ እርስ በርስ እንዲዳዳሩ/እንዱጋ፣ እነዘበርጋ ብቻ ዕቁብ እንዲጠጣጡ፣ እነጎይቶም ብቻ አገርና ድርጅት እንዲያስተዳድሩ፣ … ማድረግ እንደማይቻል ጊዜው ብዙ ትምህርት እየሰጠን ነውና ሳያመልጠን እንማርበት፡፡ በውነቱ ብዙ ከንቱነት እየተስተዋለ ነውና እባካችን ሁላችንም ማስተዋልን እንዲያድለን፣ በሰው ሰራሽ ነገሮች መለያየትንም እንድንተው በርትተን ቀን ከሌት እንጸልይ፡፡ … ፐ! ያ ሠርግ ግን አሁን ድረስ ዐይኔ ላይ አለ፡፡

([email protected])

Leave a Reply